Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ እና ጣሊያን ያላቸውን የቆየ አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር መከሩ

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሺዴ ከጣሊያን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ምክትል ሚኒስትር ኤድሞንዶ ችሬሊ ጋር ተወያይተዋል።

በአቶ አህመድ ሺዴ የተመራ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ልዑክ የኢትዮ-ጣሊያን የሁለትዮሽ ትብብርን ለማጠናከር ያለመ ውይይት ለማድረግ በጣሊያን ይገኛል።

በሮም በተደረገው ውይይት ሁለቱ ሀገራት በኢኮኖሚ ትብብር፣ በልማት አጋርነት፣ በግል ዘርፍ ኢንቨስትመንት እና ቀጣናዊ ሰላምና ውህደት ዙሪያ ያላቸውን የቆየ አጋርነት የበለጠ ለማጠናከር መክረዋል፡፡

አቶ አህመድ ሺዴ በዚህ ወቅት÷ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የተደረገውን የማክሮኢኮኖሚ ማሻሻያ ሂደትን እንዲሁም ማክሮኢኮኖሚውን ለማረጋጋት እና የኢንቨስትመንት ከባቢን ለማሻሻል እየተወሰዱ ያሉ ርምጃዎችን በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል፡፡

ጣሊያን በኢትዮጵያ በተለያዩ የልማት ዘርፎች የምታደርገውን ድጋፍም አድንቀዋል።

ኤድሞንዶ ችሬሊ በበኩላቸው÷ ኢትዮጵያ ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገትን ለማረጋገጥ የወሰደችውን የአመራር ቁርጠኝነት እንዲሁም በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን እያበረከተች ላለው አስተዋፅኦ አድናቆታቸው ገልጸዋል፡፡

ጣሊያን ኢትዮጵያ ቅድሚያ የምትሰጣቸውን የልማትና የኢኮኖሚ ዘርፎች ለመደገፍ ጠንካራ ፖለቲካዊ ቁርጠኝነት እንዳላትም አረጋግጠዋል፡፡

ጣሊያን ከኢትዮጵያ ጋር በልማት ትብብር ኢኒሼቲቮች እንዲሁም የጣሊያን ባለሃብቶችን በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የበለጠ ተሳትፎ እንዲኖራቸው ለማድረግ በትብብር መስራቷን ትቀጥላለች ማለታቸውን ሚኒስቴሩ ለፋና ዲጂታል በላከው መረጃ አመላክቷል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.