የመካከለኛው ምስራቅ ጦርነት መዘዝ እንደ ኮቪድ-19 ሊሆን ይችላል – ፕሬዚዳንት ፑቲን
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 17፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የመካከለኛው ምስራቅ ግጭት ልክ እንደ ኮቪድ ወረርሽኝ አስከፊ ሊሆን ይችላል አሉ፡፡
ፕሬዚዳንቱ የኮቪድ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት በሁሉም ሀገራት ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን አስታውሰው፥ የቀጠለው የመካከለኛው ምስራቅ አለመረጋጋትም በሀገራት ዕድገት ላይ አሉታዊ ጫና እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡
ግጭቱ በዓለም የሎጂስቲክስ፣ የምርትና አቅርቦት ሰንሰለቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ ሲሆን፥ በዚህም በነዳጅ፣ ማዕድንና የአፈር ማዳበሪያ አምራች ኩባንያዎች ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል ነው ያሉት፡፡
የጦርነቱን መጨረሻ አስቀድሞ ለመተንበይ እጅግ ፈታኝ ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ፥ የግጭቱ ተጽዕኖ የዓለምን ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ ሊያዘገይ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል፡፡
ጦርነቱ ከንጹሃን ሕልፈት በተጨማሪ የዓለምን የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚጎዳ ተናግረዋል፡፡
በዚህም ጦርነቱ በዓለም ላይ የሚያመጣውን መዘዝ ለማስቀረት የኮቪድ ወረርሽኝ ያስከተለውን ቀውስ ማስታወስ እንደሚገባ አጽንኦት መስጠታቸውን ሩሲያ ቱደይ ዘግቧል፡፡
በወንድማገኝ ጸጋዬ