Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያውያን የባሕር በር ቁጭት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ የባህር በርን አግባብ ባልሆነ መንገድ ማጣቷ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የዘመናት ቁጭት ሆኖ ቆይቷል፡፡

የባህር በርን በተመለከተ ፋና ዲጂታል ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት፥ የባህር በር ለድርድር የሚቀርብ ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡

የመዲናዋ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ሰብለ መኩሪያ የባህር በር ለሀገራችን የህልውና ጉዳይ መሆኑን ገልጸው፥ ያለአግባብ የተወሰደብንን የባህር በር በሰላማዊ መንገድ ለማስመለስ የተጀመረው እንቅስቃሴ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ሕግን ባልተከተለ መንገድ ያጣነውን የባህር በር በድርድርና የዓለምን ህግ መሰረት በማድረግ ማስመለስ ይገባል ያሉት ደግሞ ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ሀጫሉ ዋቆ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ የባህር በርን ካጣች በኋላ ወደ ሀገር ውስጥ ለምታስገባቸው ምርቶች ከፍተኛ ወጪ ለማውጣት መገደዷን ጠቁመው፤ ይህ ደግሞ የሀገርን ኢኮኖሚ ይጎዳል ብለዋል፡፡

የባህር በር ለአንድ ሀገር ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊ መሆኑን የተናገረችው ሌላኛዋ የከተማዋ ነዋሪ ሰናይት ደረጀ በበኩሏ፥ ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚ ያጣችውን የባህር በር ለማስመለስ መንግሥት የጀመረው ጥረት ተቀባይነት ያለው መሆኑን ገልጻለች፡፡

የራሳችን ሀብት ስለሆነ መመለስ አለበት ያሉት የመዲናዋ ነዋሪዎች፥ የባህር በርን ለማስመለስ የተጀመረውን ዲፕሎማሲያዊ መንገድ አድንቀዋል፡፡

የባህር በር አለመኖሩ መሰረታዊ የሆኑ ምርቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ከፍተኛ ወጪ እንደሚያስወጣ ገልጸው፥ የኑሮ ውድነትን ለመቀነስና ከድህነት ለመውጣት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ያለ አግባብ የተወሰደባትን የባህር በር ለማስመለስ የተጀመረው ጥረት ፍሬ እንዲያፈራ ሕዝቡ ከመንግሥት ጎን በመቆም ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.