ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራተጂን ለማሳካት የኒውክሌር ኃይል ሚና …
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 19፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሳንዶካን ደበበ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራተጂን ለማሳካት የኒውክሌር ኃይል የማይተካ ሚና አለው አሉ።
የኢትዮጵያ ኒውክሌር ኃይል ኮሚሽን እና የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ) ያላቸውን ስልታዊ ትብብር ለማጠናከር ተስማምተዋል።
አቶ ሳንዶካን ደበበ በኢትዮጵያ የዩኤንዲፒ ተወካይ ሳሙኤል ግባይዲ ዶን ጋር የኢትዮጵያን የኒውክሌር ኃይል መርሐ ግብር ለሰላማዊ ዓላማዎች በማዋል ረገድ በጋራ መስራት በሚቻልባቸው ስልታዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት መፍጠር የህልውና ጉዳይ መሆኑን የገለጹት አቶ ሳንዶካን፤ ወሳኝ ዘርፎችን በዘላቂነት ለመደገፍ የኒውክሌር ኃይል ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም እንደ ግብርና፣ ጤና፣ ምርምር እና ቴክኖሎጂ ያሉ ዘርፎችን እንዲሁም የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራተጂን ለማሳካት የኒውክሌር ኃይል ሚና የማይተካ ነው ብለዋል።
ዩኤንዲፒ በፈጠራ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ እና በንጹህ የኃይል አማራጮች ዙሪያ እያከናወነ ያለውን ተግባር ያብራሩት ሳሙኤል ግባይዲ ዶን በበኩላቸው፤ በቀጣይም ከኮሚሽኑ ጋር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን አረጋግጠዋል።
በዚህም በፖሊሲ ቀረጻ፣ በህዝብ ግንዛቤ ማስጨበጫ፣ ከባለድርሻ አካላት ጋር በሚደረግ ግንኙነት እና በአቅም ግንባታ ዙሪያ በጋራ ለመስራት ያለውን ዝግጁነት ገልጸዋል።
ሁለቱም ወገኖች ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ከኢትዮጵያ ማህበራዊና ባህላዊ እውነታዎች ጋር በማጣጣም በቅንጅት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።