ኮሚሽኑ ከትግራይ ክልል ባለድርሻዎች ጋር የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተሳታፊ ልየታ መርሐ ግብር ማካሄድ ጀመረ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 23፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከትግራይ ክልል ባለድርሻዎች ጋር የአጀንዳ ማሰባሰብ እና የተሳታፊ ልየታ መርሐ ግብር ማካሄድ ጀመረ።
የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር መስፍን አርዓያ (ፕ/ር) በመርሐ ግብሩ ማስጀመሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር እንዳሉት÷ የትግራይ ክልል በምክክሩ ሂደት መሳተፉ ለሀገራዊ ችግሮች መፍትሄ ለማስቀመጥ ሚናው የጎላ ነው።
ትግራይ በባህልም ሆነ በታሪክ የጠንካራ እሴቶች መገኛ መሆኑን አንስተው÷ የመድረኩ ዋና መዳረሻም ለችግሮች የጋራ መፍትሄ ማስቀመጥ ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑ በሌሎች ክልሎች እንዳካሄደው ሁሉ በትግራይ ክልልም ይህንን ለማድረግ በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቶ ዛሬ ላይ ደርሷልም ነው ያሉት።
ያለትግራይ ተሳትፎ እና አካታችነት የሀገራዊ ምክክሩ ግቡን መምታት አይችልም ያሉት ዋና ኮሚሽነሩ÷ በተለያዩ ምክንያቶች በዚህ መድረክ ተሳትፈው ሃሳባቸውን ማዋጣት ያልቻሉ አካላትን ሀሳብ ለመቀበል ሁልጊዜም ኮሚሽኑ በሩን አይዘጋም ብለዋል።
ለሦስት ቀናት በሚካሄደው መርሐ ግብር የፖለቲካ ፓርቲ እና የሃይማኖት ተቋማት ተወካዮችን ጨምሮ የተለያዩ ተቋማት ተወካዮች እየተሳተፉ ነው።
በይስማው አደራው