Fana: At a Speed of Life!

በአሰላ ከተማ በሀገራዊ ለውጡ ለተገኘው ስኬት እውቅና የሚሰጥ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ መጋቢት 24፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ሀገራዊ ለውጡ እውን የሆነበትን 8ኛ ዓመት አስመልክቶ በኦሮሚያ ክልል አሰላ ከተማ በለውጡ ለተገኘው ድልና ስኬት እውቅና የሚሰጥ ታላቅ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ እየተካሄደ ይገኛል።

በድጋፍ ሰልፉ የሐይማኖት አባቶች፣ አባ ገዳዎች፣ ሀደ ሲንቄዎችን ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

ሰልፈኞቹ በመልዕክቶቻቸው ከመጋቢት እስከ መጋቢት የተመዘገቡ የስኬት ጉዞዎችን በመግለጽ፤ በመጋቢት 24 ተምሳሌታዊ ጉዞ እና መሰረታዊ ርምጃ የተመዘገቡ ስኬቶችን አድንቀዋል።

በለውጡ መንግሥት እየተከናወኑ ያሉ የልማት ተግባራትን በመደገፍ፣ በቀጣይም የተሻለ ስራ እንዲሰራ ከመንግሥት ጋር በትብብር እንደሚሰሩ የሚያረጋግጡ መልዕክት እያስተላለፉ ይገኛል።

በዚህም በመጋቢት 24 ፍሬ ወደ ተምሳሌታዊ ጉዞ፣ ጠንካራ መሰረት የተምሳሌትነት ጉዞ ስንቅ፣ መሰረት ባለው ርምጃ ወደ ተምሳሌትነት፣ መጋቢት 24 የተምሳሌታዊነታችን መሰረትና መፍለቂያ ነው፣ የመጋቢት 24 ፍሬዎች የተምሳሌትነት ጉዞ የትውልድ ብልፅግና ነው የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።

በተጨማሪም ለውጡ የጥላቻ ሳይሆን የፍቅር ነው፣ ለሀገር ሰላምና ልማት በጋራ እንቆማለን፣ መጋቢት 24 የኢትዮጵያ ለውጥ መነሻና ብልፅግና መሠረት ነው፣ መጋቢት 24 በመስዋዕትነት መጣ በመስዋዕትነት እንጠብቀዋለን የሚሉ መልዕክቶች እየተላለፉ ነው።

የአርሲ ዞንና የአሰላ ከተማ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በለውጡ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማስቀጠል የዜጎችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከህዝብ ጋር በትብብር እየተሰራ ያለው ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በሊያ ዱጉማ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.