ኢንስትቲዩቱ በኮንስትራክሽንና ሲቪል ምህንድስና እና ግብርና ዘርፍ የቀረቡለትን 66 ደረጃዎች አጸደቀ
አዲስ አበባ፣ ሚያዚያ 16፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት በኮንስትራክሽንና የሲቪል ምህንድስና እና ግብርና ዘርፍ የቀረቡለትን 66 ደረጃዎች አጽድቋል፡፡
የኢትዮጵያ ደረጃዎች ኢንስቲትዩት ቦርድ ሚያዚያ 9 ቀን 2018 ዓ.ም ባካሄደው 5ኛ መደበኛ ስብሰባ ደረጃዎችን እንዳጸደቀ ኢንስቲትዩቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል።
በዚህም 64 ደረጃዎች በኮንስትራክሽንና የሲቪል ምህንድስና ዘርፍ የጸደቁ ሲሆን÷ ቀሪዎቹ ሁለት በምግብ ዘርፍ የተከለሱ አስገዳጅ ደረጃዎች መሆናቸው ተገልጿል።
በዚህ የምግብ ደረጃ ውስጥ በወሊድ ወቅት የሚፈጠረውን የጤና መቃወስ ለመከላከል የምግብ ጨውን በፎሊክ አሲድ ማበልፀግ የሚያስችለው አዲስ መመሪያ ጸድቋል፡፡
በኢንስትቲዩቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ ብሩክ ሀብቴ÷ የጸደቁ ደረጃዎች የዝግጅት ሂደታቸው ተገምግሞ ያለፉና ከጥራት፣ ከሰውና እንስሳት ደህንነት፣ ከአካባቢ ጥበቃና ንግድን ከማቀላጠፍ አኳያ ጉልህ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው ብለዋል፡፡
እንዲሁም በዓለም አቀፍ የንግድ ስርዓት ተቀባይነት ያላቸውን ደረጃዎችን በመጠቀም ተወዳዳሪነትን ከማሳደግ ባሻገር የገቢ ምርቶች ጥራት ቁጥጥር ወጥና ተቀባይነት እንዲኖረው የሚያስችሉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
አምራቾችና አስመጪዎች ደረጃዎች መኖራቸውን አውቀው ደረጃዎቹን በመጠቀም የምርቶቻቸውን ጥራት በማሻሻል እና ጥራታቸውን ያሟሉ ሸቀጦች ወደ ሀገር ውስጥ በማስገባት ወይም ወደ ውጪ በመላክ ለሀገር ኢኮኖሚ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉና የዜጎችን ደኅንነት እንዲያስጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።
ደረጃዎቹን ለማግኘትና ለመጠቀም ለሚፈልግ የመረጃ፣ የስልጠናና ቴክኒክ ድጋፍ አገልግሎቶችን ኢንስቲትዩቱ የሚሰጥ በመሆኑ በአገልግሎቱ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ደረጃዎቹንም ከኢንስቲትዩቱ የዶክመንቴሽን ማዕከል ማግኘት እንደሚችሉ ተገልጿል።
በምንተስኖት ሙሉጌታ