የመደመር መንግሥት መጽሐፍ የዓረብኛ ትርጉም በነገው ዕለት ይመረቃል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የተጻፈው ‘የመደመር መንግሥት’ መጽሐፍ የዓረብኛ ትርጉም በነገው ዕለት በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች አቡዳቢ ይመረቃል።
በሀገሪቱ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) እንዳሉት፤ መጽሐፉ በዋነኛነት በመካከለኛው ምሥራቅ ለሚገኙ ሁሉም ዓረብኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሀገራት፣ ሕዝቦች እና መንግሥታት በመደመር እሳቤ የምትመራዋን ኢትዮጵያን በጥልቀት የማስተዋወቅ ዓላማ አለው።
መጽሐፉ በዓረቡ ዓለም የኢትዮጵያን ፍላጎቶች እና ብሔራዊ ጥቅሞች የበለጠ ለማስጠበቅ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የመካከለኛው ምሥራቅ አድማሷን ለማስፋት የምትጠቀምበትን የጂኦ-ስትራቴጂክ እና የጂኦ-ፖለቲካ የኃይል አሰላለፍ ሚዛኑ የተጠበቀ ሆኖ እንዲቀጥል ካላት ፍላጎት አንጻር መጽሐፉ መተርጎሙን አስረድተዋል።
የመደመርን ፍልስፍና ይበልጥ ለቀጣናው ሀገራት ቅርብ በሆነ ቋንቋ ይዞ መምጣት የኢትዮጵያን ትክክለኛ ዕይታ እንደሚያሳይ ጠቁመዋል።
በመጽሐፉ ምረቃ መርሐ ግብር ላይ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ንጉሣዊ ቤተሰቦች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት ተወካዮች እንደሚገኙ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ኤምባሲ መረጃ ጠቁሟል።