Fana: At a Speed of Life!

አረንጓዴ ዐሻራ ኢትዮጵያ የተገለጠችበት ደማቅ ብሔራዊ ቀለም ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በሁሉም መስክ አቅደን የምንተገብራቸው ሕልሞቻችን እስኪሳኩ ድረስ በብርታት እንሠራለን አሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት÷ አረንጓዴ ዐሻራ ከዕሳቤ እስከ ትግበራው ኢትዮጵያ የተገለጠችበት ደማቅ ብሔራዊ ቀለም ነው።

በዕሳቤዎች የተመሩ የታላላቅ ስልጣኔዎች እና የነጠሩ እውቀቶች ማሕደር በሆነችው ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ዐሻራ እሳቤ ይህ ትውልድ የአርቆ አሳቢ አባቶቹ ልጅ መሆኑን ያስመሰከረበት የጠራ ሐቅ ነው ብለዋል።

የአየር ንብረት ለውጥ በተለምዶ ከምናየው ተደጋጋሚ የኮንፍረንስ ዕቅድ በተሻገረ፣ አፈር ነክቶ ጭቃ ረግጦ በትጋት በመስራት የሚመጣ የትጋት ውጤት መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ ከማመንጨት እስከ ትግበራ በመምራትና በመሥራት ግንባር ቀደም ሆነው አሳይተውናል ነው ያሉት።

የጠራ ዕቅድ እና መዳረሻ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ ሀገራዊ ፕሮጀክት ከታዳጊ ህጻናት ጀምሮ የእድሜ በረከት እስከበዛላቸው አረጋውያን የተሳተፉበት ታሪካዊ የልማት ዘመቻ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ልጆች ለዓመታት በስኬት የተገበሩት ይህ ኢኒሼቲቭ ሀገራችንን በዓለም ፊት በክብር እያስጠራ ያለ የለውጥ ምልክት እስከመሆን መድረሱን ጠቁመዋል።

እንደ ኮፕ 32 ያሉ ዓለም አቀፍ መድረኮችን የማስተናገድ እድሎችም በተባበረ ክንድ በተደመረ ዕሳቤ የመስራታችን ውጤቶች እና የብሔራዊ ዐሻራችን ሽልማቶች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በአረንጓዴ ዐሻራና በሌሎች የለውጥ ግቦች የታዩ የትጋት ድል ፍሬዎች በተደመሩ ጥረቶች ኢትዮጵያ በእርግጥም እየለማችና እየፈካች ትገኛለች ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ በሁሉም መስክ ታቅደው የሚተገበሩ ህልሞች እስኪሳኩ ድረስ በብርታት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.