ለሕክምና ሙከራዎች ፈቃድ የመስጠትና የቁጥጥር ሥርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ…
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) አዳዲስ የሕክምና ሙከራዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ፈቃድ የመስጠትና የቁጥጥር ሥርዓቱን ዲጂታላይዝ ማድረግ የሚያስችል ሥርዓት ተዘርግቷል አለ ጤና ሚኒስቴር።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን አዲስ የተገነባውን የሕክምና ሙከራ የኦንላይን ማመልከቻ ሥርዓት በዛሬው ዕለት አስጀምሯል፡፡
የጤና ሚኒስትር ዴዔታ ፍሬሕይወት አበበ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ ደህንነታቸውና ፈዋሽነታቸው የተረጋገጡ አዳዲስና በሙከራ ላይ የሚገኙ የሕክምና መሣሪያዎች፣ መድኃኒቶችና ሌሎች ግብዓቶች በፍጥነት ወደ ሥራ እንዲገቡ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው።
አዳዲስ የሕክምና ሙከራዎች ወደ ሥራ እንዲገቡ ፈቃድ የመስጠትና የቁጥጥር ሥርዓቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋቱን ጠቁመው ÷ይህም ለሕብረተሰቡ ጤናና ደህንነት መጠበቅ ጉልህ ሚና እንዳለው አስገንዝበዋል።
ዛሬ ይፋ የተደረገው የኦንላይን የቁጥጥር ሥርዓትም የሕክምና ሙከራዎች ፈቃድ አሰጣጥና ቁጥጥር አገልግሎትን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ የሚያደርግ መሆኑን አብራርተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ ለኢትዮጵያ የሚቀርቡ የሕክምና ሙከራ ፈቃድ አገልግሎት ጥያቄዎች እየጨመሩ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴዔታዋ÷ መተግበሪያው ሀገሪቱ የምታደርጋቸውን ዓለም አቀፍ ትብብሮች ይበልጥ ያጠናክራል ብለዋል።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሄራን ገርባ በበኩላቸው÷ አዳዲስ የሕክምና ሙከራዎች የሕብረተሰቡን ጤናና ደህንነት ለማሻሻል ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ገልጸዋል።
የሕክምና ሙከራዎች ፈቃድና ቁጥጥርን በዓለም አቀፍ መስፈርቶች መሠረት ዲጂታላይዝ ለማድረግ በተከናወኑ ተግባራት ውጤቶች እንደተገኙ መናገራቸውን ኢዜአ ነው የዘገበው፡፡
ለአብነትም የማርበርግ ቫይረስ ሕክምናን ወደ ተግባር ለማስገባት ፈጣን ምላሽና ቀልጣፋ አገልግሎት በመሰጠቱ የቫይረሱን ስርጭት መግታት መቻሉን አንስተዋል።