የኢትዮጵያን የመድሃኒት ኢንዱስትሪ አቅም ለማጠናከር…
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ፋርማኪዩር መድኃኒት ፋብሪካ ያስተዋወቃቸው ምርቶች የኢትዮጵያን የመድሃኒት ኢንዱስትሪ አቅም ለማጠናከር የሚያግዙ ናቸው አሉ የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ፍሬህይወት አበበ፡፡
የሜድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አባል የሆነው ፋብሪካው ለሕፃናት ሕክምና ወሳኝ የሆኑ ሰባት አዳዲስ ምርቶችን በይፋ አስተዋውቋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ እነዚህ ምርቶች በሀገር ውስጥ መመረታቸው ለጨቅላ ሕፃናት ጭምር ደረጃቸውን የጠበቁ ምርቶች እንዲኖሩ የሚያስችል ነው።
በኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ያለውን የውጭ ጥገኝነት የሚቀንስና የጨቅላ ሕፃናትን ሕይወት ለመታደግ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ምርቶቹ መንግሥት አክሞ የማዳን አቅምን መሠረት በማድረግ ለቀረጸው ፖሊሲና ኢትዮጵያ በአፍሪካ የመድሃኒት አቅርቦት ማዕከል ለመሆን የምታደርገውን ጉዞ የሚያግዝ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
የፋርማኪዩር መድኃኒት ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰለሞን ገብረአማኑኤል በበኩላቸው፥ የፋብሪካው ግንባታና የቴክኖሎጂ አቅም ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን የጠበቀ መሆኑን አመልክተዋል።
ምርቶቹ ሙሉ በሙሉ በራስ አቅምና እውቀት የተመረቱ መሆናቸውን ገልጸው፥ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ያድናሉ ነው ያሉት፡፡
የፔዲያትሪክ አይቪ ፈሳሾች በቀጥታ በደም ሥር የሚሰጡ የሕክምና መፍትሔዎች ሲሆኑ፥ በሕመምና በድርቀት ምክንያት የሚከሰቱ የፈሳሽና የስኳር እጥረቶችን በፍጥነት በመተካት የጨቅላ ሕፃናትን ሕይወት ለመታደግ የሚያገለግሉ መሆናቸው ነው የተገለጸው፡፡
በአንዱዓለም ተስፋዬ