Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀን….

ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ገዢዎች ነጻ እንዲወጡ፣ ለአሁኑ የአፍሪካ ሕብረት እና ለቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ምሥረታ ያበረከተችው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡

በአፍሪካውያን መካከል እህትማማችነትና ወንድማማችነት እንዲጎለብት ኢትዮጵያ በሕገ መንግሥቷ አንቀጽ 86(5) ላይ እውቅና ሰጥታለች፡፡

ይህም ሀገሪቷ ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ጋር በየጊዜው እያደገ የሚሄድ ኢኮኖሚያዊ ሕብረትና የሕዝቦች ወንድማማችነትን ማጎልበት የሚያስችል ነው፡፡

አንቀጽ 86(5) የኢትዮጵያን የውጭ ግንኙነት መርሕ ያስቀምጣል፡፡ ሀገራችን በሕገ መንግሥቷ ባስቀመጠችው መሠረት ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን አጋርነት ለማሳደግ፣ ለፓን አፍሪካኒዝም እና ለአፍሪካ የውህደት አጀንዳ ተግባራዊነት ያላትን ቁርጠኝነት አሳይታለች፡፡

በሕገ መንግሥቷ ለአፍሪካ ሕብረት አንድነት የሰጠችውን ትኩረት የሚያጠናክሩ በርካታ ተግባራትንም አከናውናለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሐምሌ 9 ቀን 2012 ዓ.ም ስራ ላይ ያዋለችው አዋጅ ቁጥር 1209/2012፣ የአፍሪካ ኅብረት ሰንደቅ ዓላማ፣ መዝሙርና የአፍሪካ ቀንን በተመለከተ የሚደነግግ ነው፡፡

ይህም ሀገራችን ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን አጋርነት ለማሳደግ፣ ለፓን አፍሪካኒዝምና ለአፍሪካ የውህደት አጀንዳ ተግባራዊነት ያላትን ቁርጠኝነት ለማስቀጠል ያለመ ነው፡፡

አዋጁ ኢትዮጵያ ለሕብረቱ ኮሚሽን የአስተናጋጅ ሀገርነት ሚናዋን ለመወጣት ከምታከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ የአፍሪካ ሕብረት ሰንደቅ ዓላማ እንዲውለበለብ፣ የአፍሪካ ሕብረት መዝሙር እንዲዘመር እና የአፍሪካ ቀን ታስቦ እንዲውል የሚያደርግ ነው፡፡

ይህም ሀገራችን ለሕብረቱ ያላትን ቁርጠኝነት የሚያሳይ በመሆኑ በአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባዔ የሕብረቱ ሰንደቅ ዓላማ እና መዝሙር በአባል ሀገራት እንዲውለበለብ እና እንዲዘመር እንዲሁም የአፍሪካ ቀን እንዲከበር ያስተላለፈውን ውሳኔ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ የሕግ ማዕቀፍ በማስፈለጉ የጸደቀ አዋጅ ነው፡፡

የአፍሪካ ቀን ከቅኝ ግዛት ቀንበር መላቀቅ ያቃታቸው አፍሪካውያን ባሉበት የተስፋ ዜናን የሰሙበት፣ የነፃነት አየር የሚተነፍሱ አፍሪካውያንም በአንድነት ለአንድ ዓላማ መሠለፍ የቻሉበት ቀን ነው፡፡

መጀመሪያ አንድነቱ ተስፋ ነበር፤ ተስፋውም የነፃነት ትግሉን እያሰፋ አፍሪካን ነፃ አወጣ፡፡

ዲፕሎማሲያዊና ወታደራዊ አቅምን በማስተባበር አፍሪካውያንን ለድል አብቅቷል፡፡

ይህ የታሪክ እውነታ ነው የአፍሪካ ቀን በአፍሪካና ጥቁሮች በሚኖሩባቸው የዓለማችን ክፍሎች ሁሉ በደማቅ እንዲከበር ያደረገው፡፡

ደቡብ አፍሪካ ይህንን ወር የአፍሪካ ወር በሚል ሰይማዋለች፡፡ እንደነ ዚምባቡዌ፣ ማሊ፣ ናሚቢያ፣ ጋምቢያ፣ ዛምቢያ፣ ሞሪታኒያ፣ ሌሶቶ እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ደግሞ የአፍሪካ ቀንን በብሔራዊ በዓልነት ያከብራሉ፡፡

የአፍሪካ ቀን እንደየሀገራቱ በተለያዩ ፕሮግራሞች ይከበራል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.