በክልሉ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት ክፍት ሆኑ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነቡ የልማት ፕሮጀክቶችን መርቀው ለአገልግሎት ክፍት አድርገዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ከተማ ተገኝተው ፕሮጀክቶቹን አገልግሎት ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት፥ ፕሮጀክቶቹ የሕዝቡን የቆየ የልማት ጥያቄ የሚመልሱ ናቸው፡፡
በዛሬው ዕለት ለአገልግሎት የበቁት የልማት ፕሮጀክቶቹ የአካባቢውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር ታስበው የተገነቡ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ከተመረቁት ፕሮጀክቶች መካከል የተለያዩ ቀበሌዎችን እርስ በርስ የሚያገናኙ ድልድዮችና የከተማዋን ገጽታ የሚቀይር የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክት ይገኙበታል።
እነዚህ መሰረተ ልማቶች በአካባቢው ያለውን የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ከማቃለላቸውም በላይ ለነዋሪዎች ምቹና ውብ የመዝናኛ ስፍራዎችን እንደሚፈጥሩ ነው የተገለጸው።
በተጨማሪም የነዋሪዎችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥና የገበያ ትስስርን ለመፍጠር የተገነባው የማር፣ የወተት እና የእንቁላል መሸጫ ማዕከል ተመርቆ ተከፍቷል፡፡
ማዕከሉ ለአካባቢው አምራቾች ሰፊ የገበያ ዕድል በመፍጠር ለተጠቃሚው ማህበረሰብ ንጹህና አልሚ ምግቦችን በቀላሉ እንዲያገኝ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
በመለሰ ታደለ