ለጠላት የተሳሳተ ስሌት ምላሽ ለመስጠት ጦሩ በተጠንቀቅ ቆሟል – ኢራን
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 5፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ የኢራን ጦር በጠላት ለሚሰነዘር ማንኛውም ጥቃት አስተማማኝ ምላሽ ለመስጠት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ ነው አለ።
ቴህራን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አሁን ጠንካራ፣ ዝግጁ እና በቀላሉ የማትደናቀፍ ሆናለች ሲል የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ኢራን በጠላት እንቅስቃሴዎች ላይ የተሟላ የመረጃ የበላይነት የያዘች እና ለየትኛውም የጠላት እንቅስቃሴ ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚያስችል ሙሉ ዝግጅት እንዳላትም አስገንዝቧል።
አሜሪካና እስራኤል በኢራን ክብር፣ ነጻነት እና የእድገት ጎዳና ላይ ያነጣጠሩ የወታደራዊ፣ ስለላ፣ ሚዲያ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቃቶችን ቢሞክሩም፤ ይህ የተሳሳተ ስሌት ሳይሳካ ቀርቷል ነው ያለው መግለጫው።
የኢራን እና የአሜሪካ ግጭት በአሁኑ ወቅት እየተባባሰ የመጣ ሲሆን÷ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በቅርቡ የኢራን ዋነኛ የነዳጅ ማስተላለፊያ የሆነውን ኻርግ ደሴትን እቆጣጠራለሁ ማለታቸው ይበልጥ አወሳስቦታል።
ከሰሞኑ አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት መፈጸሟን ተከትሎ የኢራን ጦር በአካባቢው በሚገኙ የአሜሪካ ኃይሎች ላይ የአጸፋ ጥቃት መፈጸሙ ይታወቃል።
አሁን ላይ ደግሞ ኢራን እና አሜሪካ እያካሄዱት ባለው የሰላም ስምምነት ዙሪያ እርስ በርሱ የሚጣረስ መረጃ እያወጡ ይገኛሉ፡፡
ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኢራን ጋር የሚደረገው ውይይት መሻሻል በማሳየቱ ኢራን ላይ የሚፈጸመው ጥቃት መቆሙን ተናግረዋል፡፡
ኢራን በበኩሏ ውስብስብ የሆነው የሀገራቱ ስምምነት ገና እንዳልተቋጨ ይፋ ማድረጓን የቢቢሲና ፕሬስ ቲቪ ዘገባ ያመላክታል፡፡
በብርሃኑ አበራ