Fana: At a Speed of Life!

በምርጫው የታየው የሕዝቡ የሰላምና የብልጽግና ጉጉት ትልቅ የኃላፊነት አደራ ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ ሕዝብ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ወቅት ያሳየው ከፍተኛ የሀገር ፍቅር፣ የሰላምና የብልጽግና ጉጉት ትልቅ የኃላፊነት አደራ ነው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በተለያዩ ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን በአንድ መድረክ የሚያጣምረውን የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት ÷ በኢትዮጵያ የተመዘገቡት አመርቂ የልማት ጅማሮዎች እና ውጤቶች የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ደስታ ናቸው ብለዋል።
ይሁንና የተጀመሩት አበረታች ስኬቶች የመጨረሻ ግብ ሳይሆኑ አገልግሎትን ይበልጥ ለማሻሻልና የሕብረተሰቡን እርካታ ለማሳደግ እንደ ትልቅ ማበረታቻ የሚወሰዱ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ ሕዝብ በምርጫው ወቅት ያሳየው ከፍተኛ የሀገር ፍቅር፣ የሰላምና የብልጽግና ጉጉት ትልቅ የኃላፊነት አደራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሕዝብ ይህንን ዕድል የሰጠው የቴክኖሎጂና የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎቶች ተሻሽለው፣ ሌብነት ቀንሶ፣ ልማት ተፋጥኖ ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል ይፈጠራል በሚል ጽኑ እምነት በመሆኑ ሁሉም ይህንን እምነት በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜትና በታማኝነት ሊመልሰው እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
እስካሁን የተከናወኑት ተግባራት እጅግ አበረታች ናቸው፤ በተለይም መሶብን ከአንድ ማዕከል ወደ ተንቀሳቃሽ አውቶቡስ ሥርዓት እንዲሁም ወደተቀናጀ መተግበሪያ ማሸጋገር መቻሉ ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል።
ይህ አስደማሚ የዲጂታል ዕድገት በሀገር ውስጥ ብቻ የሚገደብ ሳይሆን ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት እንዲሰፋ ትልቅ ራዕይ ተቀምጧል ነው ያሉት።
በቀጣይ ቴክኖሎጂውን ለሌሎች ሀገራት በማስተማር፣ በመሸጥና ወደ ኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪና ገቢ በማስገባት ረገድ ሰፊ ሥራዎች እንደሚጠበቁ አመልክተዋል።
በየተቋማቱ የሚታዩ የአገልግሎት መጓተቶችንና የብልሹ አሰራር ፈተናዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ቴክኖሎጂን በሰፊው ጥቅም ላይ ማዋልና የሕዝብን ችግር በቅንነት መቅረፍ የሁሉም የሥራ ኃላፊዎች ቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሶስና አለማየሁ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.