ሀገር አሻጋሪ ተቋማት ግንባታ …
ለዛሬው ታይታ ሳይሆን ለነገው ትውልድ የሚያስብ መንግሥት ለተቋማት ግንባታ ይጨነቃል፡፡
ግለሰቦች ጥሩ ሀሳብ ቢኖራቸውም ተቋማዊ ካልሆኑ ዘመናትን አይሻገሩም፡፡
ሀገርን በዘላቂነት የሚያሻግሩት ተቋማት በመሆናቸው ኢትዮጵያ በዚህ ላይ እየሰራች ነው፡፡
መንግሥት ሀገር እንድትሻገር መጀመሪያው ያደረገው የፖለቲካ ቁርጠኝነትን ማረጋገጥ ነው፡፡
ቁርጠኛ በመሆኑም የሕግ ማሻሻያዎችን በማድረግ ነጻና ገለልተኛ ተቋማት እንዲፈጠሩ ምክንያት ሆኗል፡፡
ይህም ተቋማት ሥራቸውን ያለጣልቃገብነት እንዲከውኑ አግዟቸዋል፡፡
የፋይናንስ፣ የሎጂስቲክስ እና የሰው ኃይል ነጻነት ኖሯቸው በገለልተኛ ሰራተኞች እንዲሰሩም እያደረገ ይገኛል፡፡
ዓመታትን እና ስርዓቶችን የሚሻገሩ ተቋማትን ቀድመው የገነቡ ሀገራት በዘመናት መካከል ግለሰቦች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ሥርዓቶች ቢቀያየሩም፣ ወደ ስልጣን የሚመጣው አካል የቀድሞውን አሻራ አጥፍቶ የራሱን አዲስ በመገንባት ጊዜውን አያባክንም፡፡
ከነባሩ ጠቃሚውን ወረት ወስዶ ጊዜው የደረሰበትን አዳዲስ አስተሳሰብ በማከል በሀገር ግንባታ ላይ ትኩረቱን ያደርጋል፡፡
በኢትዮጵያ ስርዓቶች መጥተው ሲሄዱ አሻራቸው እንዲደበዝዝና እንዲጠፋ ሲደረግ ኖሯል፡፡
እንደ አዲስ ስልጣን የሚይዘው አካል የቀድሞውን እንደ ወረት ከመጠቀም በመቅበር ላይ ያተኩር ነበር፡፡
በዚህ አይነት አዙሪት በርካታ ጠቃሚ አስተሳሰቦችና የሀገር ቅሪቶች እንዲረሱ ሆኗል፡፡
አካሄዱ ጎጂ መሆኑን የተረዳው የለውጡ መንግሥት መልካሙን በመውሰድ አዳዲስ ነገሮችን በመደመር፣ ትምህርት ሊሆን የሚገባው እንዳይደገም በማድረግ ሀገረ መንግሥት ግንባታውን ተያይዞታል፡፡
ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ተቋማት ወሳኝ ናቸው፡፡
በሰው አዕምሮ ውስጥ ብቻ ያለ ሀሳብ እየደበዘዘ በጊዜ ብዛት ይጠፋል፡፡
ሀሳቡ ሀገር አሻጋሪ ጠንካራ ተቋማት ላይ ያረፈ ከሆነ ግን ቀጣይ ትውልድ እንደ እርሾ ይጠቀምበታል፡፡
ጠንካራ፣ ውጤታማ እና ዘላቂነት ያላቸውን ተቋማት ወይም መዋቅሮችን መፍጠር ለአንድ ማህበረሰብ ወይም ሀገር ወሳኝ ነው፡፡
የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና የማህበራዊ እድገትን ለማረጋገጥ ይረዳሉ፡፡
አስተማማኝ አሰራር ያላቸው ተቋማት ለሀገሪቱ ምቹ የኢኮኖሚ ሁኔታን በመፍጠር ዘላቂ የልማት ግቦች እውን እንዲሆኑ ያግዛሉ።
የተቋማት ግንባታ አሰራር በግልጽ ራዕይ እና ተልዕኮ፣ ህጋዊ መዋቅር፣ የሰው ኃይል ልማት፣ በቴክኖሎጂ የዘመነ አሰራር፣ ግልጽነትንና ተጠያቂነት፣ ቀጣይነትን፣ የተሻሻለ አገልግሎት፣ እምነት የተገነባበት እና ኢንቨስትመንት የሚሳብበት እንዲሆን ያስችላል፡፡
ግልፅነትና ተጠያቂነት ያላቸው ተቋማት ሙስናን እና ብልሹ አሰራሮችን በመከላከል መንግሥታዊ አገልግሎቶች ተደራሽና ውጤታማ እንዲሆኑ ያደርጋሉ።
ከተቋማትም የዴሞክራሲ ተቋማትን መገንባት ደግሞ የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ ሰብአዊ መብቶችን ለማስከበር እና የዜጎችን እኩል ተሳትፎ ለማረጋገጥ ወሳኝ ያደርጋቸዋል።
እነዚህ ተቋማት ገለልተኛ ናቸው፡፡ ይህ አሰራርም ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ ያደርጋል፡፡
በዴሞክራሲ ተቋማት ግንባታ የምርጫ ቦርድ ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ነፃ፣ ገለልተኛ፣ ዴሞክራሲያዊ እና እውነተኛ ምርጫን ለማካሄድ ያስችላል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም በዚሁ መሠረት የ7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ እንዲካሄድ ሚናውን ተወጥቷል፡፡
በምርጫው ሂደት የስልጣን ምንጭ የህዝብ ድምጽ ይሁንታ እንጂ ጠብ መንጃ ያለመሆኑን ምርጫ ቦርድ በተግባር አረጋግጧል።
በሀገራችን በሚደረገው የተቋማት ግንባታ ገለልተኛ የፍትሕ ተቋማት እየተፈጠሩ ይገኛሉ፡፡
በዚህ ሂደት ፍርድ ቤቶች እና የሕግ አስከባሪ አካላት በነጻነት እንዲሰሩ ተደርጓል፡፡
በምርጫ ወቅትም በነጻነት ክትትል በማድረግ ያለ አድልዎ በማገልገል የሂደቱን ዴሞክራሲያዊነት አረጋግጠዋል፡፡
ጠንካራ የፍትህ፣ የፀጥታና የዴሞክራሲ ተቋማት አድልዎ የሌለበት ፍትሕ በመስጠት የዜጎችን እኩልነትና ሰብአዊ መብት ያስከብራሉ።
በስምንት ዓመታት የተቋማት ግንባታ ውስጥ ነጻነቱን ያወጀው ሌላኛው ተቋም የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ነው፡፡
ተቋሙ ነጻ ሆኖ የመብት ጥሰቶችን በመከታተል ለፍትሕና ርትዕ እየሰራ ይገኛል፡፡
በተመሳሳይ ስራ ላይ የሚገኘው የሀገራችን የዕንባ ጠባቂ ተቋም የመልካም አስተዳደር እጥረቶች እና የሙስና ጉዳዮችን በመመርመር በገለልተኛነት ለሀቅ እየሰራ ነው፡፡
መንግሥት በተቋማት ግንባታ ሂደት ባካሄደው ሪፎርም የመገናኛ ብዙኃን ነፃ ሆነው ለሕዝብ ትክክለኛ መረጃ እንዲያደርሱ ተደርጓል፡፡
አሰራሩ ተቋማቱ በህዝብ እና በመንግሥት መካከል ሚዛናዊ የመረጃ ድልድይ ሆነው እንዲያገለግሉ መንገድ ከፍቷል፡፡
በመሆንም የመንግሥትን አሰራር ፈትሸው የሚታረመው እንዲስተካከል፤ የሚበረታታው ሞዴል እንዲሆን በማሳየት ያቀርባሉ፡፡
የፀጥታ ተቋማት ገለልተኛ ሆነው እንዲገነቡ፣ ሁሉንም እኩል እንዲያገለግሉ፣ ከግለሰብ እና ከፓርቲ ህልውና በላይ ለሀገር እንዲቆሙ አድርጓቸዋል፡፡
ጠንካራ የመከላከያና የደህንነት ተቋማት የሀገርን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ባለፈ የዜጎችን ደህንነት አስተማማኝ በማድረግ ሀገር እንድትቀጥል መሠረት ይሆናሉ።
እንደነዚህ አይነት ተቋማትን መገንባት የስልጣን ሚዛንን ለመጠበቅ፣ ተጠያቂነትን ለማስፈን፣ ግልጽነትን ለመፍጠር፣ የዜጎችን እምነትና ተሳትፎ ለማሳደግ ወሳኝ ናቸው፡፡
በሕግ አውጪ፣ ተርጓሚ እና አስፈጻሚ መካከል የስልጣን ሚዛንን በመጠበቅ ቁጥጥር ያደርጋሉ፡፡
ሕዝቡም በሕግ እና በአስተዳደር ሥርዓቱ ላይ እምነት እንዲኖረው ያስችላሉ፡፡
በአጠቃላይ የተቋማት ግንባታ የሀገረ መንግሥት ግንባታ ዋና ምሰሶ ነው፡፡
የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥ፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለመገንባት እንዲሁም የተረጋጋና ዘላቂ ሀገርን ለመፍጠር ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡
ተቋማት በግለሰቦች ፍላጎት ሳይሆን በህግና ስርዓት የሚመሩ ሲሆኑ፣ ከመንግሥት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚመጡ አላስፈላጊ ጫናዎችንና የፖለቲካ አለመረጋጋቶችን ይከላከላሉ።
ኑ፤ ሀገር እንገንባ!