የዚምባብዌው ዛኑ-ፒኤፍ ፓርቲ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፈ
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 25፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የዚምባብዌው ገዥ ፓርቲ ዛኑ-ፒኤፍ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ለብልጽግና ፓርቲ እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል፡፡
የኢትዮጵያ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ ከእህት የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ከዓለም አቀፍ አጋሮች ይፋዊ የእንኳን ደስ አላችሁ መግለጫዎችና ደብዳቤዎች እየተላኩ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ መረጃ አመልክቷል፡፡
ይህ ሰፊ ዓለም አቀፍ እውቅናም ኢትዮጵያ ያስመዘገበችውን እና የደረሰችበትን ወሳኝ የዴሞክራሲ ምዕራፍ የሚያንጸባርቅ መሆኑን የብልጽግና ፓርቲ መረጃ አመልክቷል፡፡
የዚምባብዌ አፍሪካ ብሔራዊ ህብረት-የአርበኞች ግንባር (ዛኑ-ፒኤፍ) ምርጫው በስኬት በመጠናቀቁ ለብልጽግና ፓርቲ ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ለብልጽግና ፓርቲ እና ለኢትዮጵያ ሕዝብ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
ዛኑ-ፒኤፍ ባስተላለፈው መልዕክት የኢትዮጵያ ምርጫ በስኬት መጠናቀቅ ሀገሪቱ ለሰላም፣ ለመረጋጋት እና ለሕዝቦቿ ሉዓላዊ ፈቃድ ያላትን ጽኑ ቁርጠኝነት የሚያሳይ የዴሞክራሲ ምዕራፍ ነው ብሏል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ ያገኘው ሰፊ የሕዝብ ውክልና ኢትዮጵያውያን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አመራር እንዲሁም አካታች ልማትን፣ ብሔራዊ አንድነትንና ቀጣናዊ ውህደትን ለማምጣት ባላቸው ራዕይ ላይ ያላቸውን እምነት የሚያሳይ መሆኑን አውስቷል።
በሁለቱ እህት ፓርቲዎች እና ሀገራት መካከል ያለውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት የገለጸው ዛኑ-ፒኤፍ ÷ ኢትዮጵያ አፍሪካ የራሷን ዕድል በራሷ ለመወሰንና የኢኮኖሚ ነጻነትን ለማግኘት ለምታደርገው ጥረት ታማኝ አጋር መሆኗን ገልጿል።
በተጨማሪም የዚህ ምርጫ ስኬት የፓን-አፍሪካኒዝም አብሮነትን እንደሚያጠናክርና የአፍሪካ ኅብረት የ2063 አጀንዳ የጋራ ግብን እንደሚያሳይ አጽንኦት ሰጥቷል።
ዛኑ-ፒኤፍ ሁለቱ ፓርቲዎችና ሀገራት ለሕዝቦቻቸው ብልጽግና፣ አንድነት እና ክብር በጋራ መስራታቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጾ÷ በመካከላቸው ያለውን የወንድማማችነት ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ቁርጠ መሆኑን አረጋግጧል።