Fana: At a Speed of Life!

መንግሥት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከየትኛዉም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነዉ – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሰኔ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፈታተን ነገር ከመጣ መንግሥት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከየትኛዉም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነዉ አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ለምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) በሰጡት ምላሽ እንዳሉት፤ የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተከትሎ በትግራይ ጊዜያዊ መንግሥት ተቋቁማል።

ከ60 ሺህ በላይ ታጣቂዎች አስፈላጊው ድጋፍ መደረጉን ጠቁመው፤ ትጥቅ የማስፈታት፣ የማቋቋምና ወደ ህብረተሰቡ የመመለስ ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት፡፡

ስምምነቱ ለትግራይ ህዝብ እፎይታን ሰጥቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከጦርነቱ በፊትና በጦርነቱ ጊዜ ተቋርጠው የነበሩ አገልግሎቶች ሙሉ በሙሉ መመለሳቸውን ገልጸዋል፡፡

በትግራይ ክልል ሰላም እያወኩ ያሉ ጥቂቶች መሆናቸውን አንስተው፤ ሰላም የሚያውኩ ኃይሎች ቤተሰቦቻቸውን ከፊሎቹን በአዲስ አበባ ቀሪዎቹን ደግሞ በውጪ ሀገራት ያስቀመጡ ናቸው ብለዋል፡፡

ትግራይ መውደም ነበረባት ብለው የሚያምኑ ኃይሎች ከፕሪቶሪያ ስምምነት በኋላ ማኩረፋቸውን ገልጸው፤ በአክራሪ ኃይሎች በየቀኑ ጦርነት ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ትንኮሳዎች እንደሚፈጸሙ ጠቁመዋል፡፡

የትግራይ ወጣቶች በጉልበት ታፍነዉ ለሱዳን ኃይሎች መሸጣቸውን ገልጸው፤ እነዚህ ወጣቶች ምንም ለማያውቁት ጦርነት ህይወታቸውን እያጡ ነው ብለዋል።

የትግራይ ህዝብ የችግሩ ባለቤት ሳይሆን ገፈት ቀማሽ መሆኑን አመልክተው፤ አሁን ላይ በትግራይ ውስጥ ከሚኖር የትግራይ ተወላጅ በላይ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎች ያሉ የትግራይ ወላጆች በሰላም እና በነጻነት ህይወታቸውን እየመሩ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚፈታተን ነገር ከመጣ መንግሥት የሀገሪቱን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ ከየትኛዉም ጊዜ በላይ ዝግጁ ነው ብለዋል።

በወንድማገኝ ጸጋዬ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.