ከ3 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገው የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ፕሮግራም…
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 3፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም ከ3 ሚሊየን በላይ ዜጎች ተጠቃሚ ሆነዋል አሉ የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ፡፡
የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም የፌዴራል ስትሪንግ ኮሚቴ ዓመታዊ ጉባዔ እየተካሄደ ነው፡፡
ጫልቱ ሳኒ በዚህ ወቅት እንዳሉት ÷ የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮግራም የገጠር ትራንስፎርሜሽንን እያፋጠነ ይገኛል፡፡
ፕሮግራሙ በገጠር የመንገድ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን በማፋጠንና የገጠር ትራንስፎርሜሽንን በማሳካት በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው ብለዋል፡፡
በፕሮግራሙ በተያዘው በጀት አመት 1 ሺህ 123 ፕሮጀክቶች መከናወናቸውን ጠቁመው ÷ በዚህም ከ3 ሚሊየን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡
የገጠር ትስስርና ተደራሽነት ለምግብ ዋስትና ፕሮጀክት በዓለም ባንክ እና በክልሎች መዋጮ የሚመራ እና ለዜጎች ምርትና ምርታማነት የሚሰራ ፕሮጀክት ነው፡፡
በሀና ታደሰ