Fana: At a Speed of Life!

የነዋሪዎቿን የዕለት ተዕለት ኑሮ ምቹ፣ ጤናማ እና ዘመናዊ ከማድረግ እስከ ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት

አዲስ አበባ የነዋሪዎቿን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል እና ገጽታዋን ለመቀየር ዘርፈ ብዙ ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን አከናውናለች።

እነዚህ ስራዎች በዋናነት የከተማ መሠረተ ልማትን ማዘመን፣ የኑሮ ውድነትን ማቃለል እና ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የህብረተሰብ ክፍሎች መደገፍ ላይ ያተኮሩ ናቸው።

የከተማዋን መልክ ሙሉ በሙሉ የቀየረውና ነዋሪዎች ዘመናዊና ምቹ የከተማ ህይወት እንዲመሩ ያስቻለው የኮሪደር ልማት የእነዚህ አንዱ ትልቁ ማሳያ ፕሮጀክት ነው።

በዚህም ሰፋፊ የእግር ጉዞ መንገዶች እና ከ100 ኪሎ ሜትር በላይ የብስክሌት መስመሮች ተገንብተዋል።

ከ70 በላይ አረንጓዴ ፓርኮች፣ የህጻናት መጫወቻዎች እና ከ120 በላይ ዘመናዊ የህዝብ መጸዳጃ ቤቶችም ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።

በምሽት የነዋሪዎችን ደህንነት ለመጠበቅና የከተማዋን የ24 ሰዓት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ለማገዝ ዘመናዊ መብራቶችና የደህንነት ካሜራዎች የተገጠሙባቸው ስማርት ፖሎች ተተክለዋል።

በከተማዋ የኑሮ ውድነት በዝቅተኛው የህብረተሰብ ክፍል ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ ከተማ አስተዳደሩ የተለያዩ አማራጮችን እየተገበረ ይገኛል።

አምራቹንና ሸማቹን በቀጥታ የሚያገናኙ ዘመናዊ የገበያ ማዕከላትን በከተማዋ መግቢያዎች ላይ ገንብቷል።

በተጨማሪም የቅዳሜና የእሁድ ገበያዎች እና የሸማቾች ማህበራት በስፋት ተንቀሳቅሰዋል።

ነዋሪዎች በየመኖሪያቸውና በየተቋማቱ የጓሮ አትክልት፣ የዶሮ እና የእንስሳት እርባታ ላይ እንዲሰማሩ በመደረጉ በምግብ ራስን ለመቻል የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት አግዟል።

መንግሥት በቢሊዮን የሚቆጠር ብር በመመደብ እንደ ስንዴ፣ ዘይት እና ስኳር ያሉ መሰረታዊ ሸቀጦች በቅናሽ ዋጋ ለህብረተሰቡ እንዲቀርቡ አድርጓል።

የከተማዋ ልማት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ፍትሀዊ በሆነ መልኩ ተጠቃሚ እንዲያደርግ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷል።

ለተማሪዎች የዕለት ምገባ እና የትምህርት ቁሳቁስ በነጻ ማቅረብ ተጠናክሮ ቀጥሏል። ይህ ተግባር የወላጆችን የኢኮኖሚ ጫና በከፍተኛ ደረጃ ቀርፏል።

በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ነዋሪዎች እና አቅመ ደካሞች የሚኖሩባቸውን አሮጌ ቤቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ የማደስና የማስዋብ ሰፊ ዘመቻ ተካሂዶ ሰውን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

በተጨማሪም በበዓላት እና በተለያዩ ወቅቶች ለአቅመ ደካሞች እና አረጋውያን የምግብ ቁሳቁስ ድጋፍ የማድረግ ልማድ ባህል ሆኖ ቀጥሏል።

በከተማዋ የትራንስፖርት መጨናነቅን ለመቀነስ እና ንፅህናን ለመጠበቅ ሰፊ ስራዎች የተሰሩ ሲሆን፣ በርካታ አዳዲስና ዘመናዊ የአውቶቡስና የታክሲ ተርሚናሎችም ተገንብተዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎች በስፋት በከተማዋ በመዘጋጀታቸው ከተማዋ ለመዘመን የያዘችውን አይቀሬ የእቅድ ትግበራ ቁርጠኝነት አሳይታለች።

ከዚህ ቀደም የተበከሉና ለጎርፍ ተጋላጭ የነበሩ የወንዝ ዳርቻዎች ተገንብተው ወደ ጽዱ፣ ውብ እና ለህዝብ ክፍት ወደሆኑ የመዝናኛ ስፍራዎች ተቀይረዋል።

በአጠቃላይ፣ በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ የልማት ስራዎች የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ከማሳደጋቸውም በላይ፣ የነዋሪዎቿን የዕለት ተዕለት ኑሮ ምቹ፣ ጤናማ እና ዘመናዊ በማድረግ ረገድ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣት ችለዋል።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.