አየር ኃይላችን በማንኛውም ሁኔታ ኢትዮጵያን የመጠበቅ አቅም ገንብቷል – ሌ/ጄ ይልማ መርዳሳ
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ አየር ኃይላችን በማንኛውም ሁኔታና ጊዜ ኢትዮጵያን በሙሉ አቅሙ የመጠበቅ ግዳጁን በጀግንነት ለመወጣት የሚያስችል አስተማማኝ የዝግጁነት አቅም ገንብቷል አሉ።
አየር ኃይሉ የዘላቂ ተቋም ግንባታ ላይ ትኩረት አድርጎ በመስራቱ አመርቂ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።
ሠራዊቱ በስነ-ልቦና፣ በቴክኖሎጂ እና በዝግጁነት አቅሙ የኢትዮጵያን ሰላም የሚያስጠብቅ ድል አድራጊ ኃይል ሆኖ እንደሚቀጥል አጽንኦት ሰጥተዋል።
ተቋሙ በዘመናዊ ትጥቅና በላቀ የሰው ኃይል ስልጠና ሠራዊቱን ማደራጀት መቻሉንና በስልጠናው የተገኘው እውቀትና ቴክኖሎጂም ሠራዊቱ ግዳጁን በብቃት እንዲወጣ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
የአየር ኃይሉ የሪፎርም ስኬቶች በተግባር መታየታቸውን አንስተው፤ ተቋሙ በተለያዩ ቦታዎች ታላላቅ ተልዕኮዎችን የመፈጸም የዝግጁነት አቅም መገንባቱን አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቁ በርካታ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅምና በአነስተኛ ወጪ ማከናወን መቻሉን አመልክተዋል።
እንዲሁም የአቪዬሽን ከባድ ጥገና ማዕከሉ አቅም አድጎ የሌሎች አውሮፕላኖችን ጥገና ፍቃድ ማግኘቱ የቴክኖሎጂ እድገታችንን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ማዕከሉ ለምድር ኃይሉ የትራንስፖርትና የውጊያ ድጋፍ በማድረግ፣ በኦፕሬሽናል እና ታክቲካል ውጊያዎች ድል አድራጊ ኃይል መፍጠሩን አጽንኦት መስጠታቸውን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ለፋና ዲጂታል የላከው መረጃ ያመላክታል።