በታላቅ የድል ዋዜማ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ …
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 7፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ በሰላማዊ ውይይትና ሀገራዊ መግባባት የገጠማትን ችግር ለመፍታት የሀገራዊ ምክክር ጉዞ ላይ ትገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ የጀመረችው የሀገራዊ ምክክር ሂደት የሕዝብን ድምፅ ከመሰብሰብ ወደ ተጨባጭ የፖሊሲ እና የሀገራዊ መግባባት ምክረ ሃሳቦች የሚሸጋገርበት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
በኢትዮጵያ ያለው የችግር ቋጠሮ ሊፈታ የሚችለው በንግግርና ምክክር ብቻ ሲሆን፤ሀገራዊ ምክክሩ አሁን ላይ ወደ ዋናው ምዕራፍ ተሸጋግሯል፡፡
ጉባኤው ግን በተሰባሰቡ እና በተቀረጹ አጀንዳዎች ላይ ተመስርቶ መግባባት ላይ የሚደረስበት ነው። ጉባኤው የሃሳብ ነፃነት እና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ማዕከል በማድረግ፣ በአጀንዳዎቹ ላይ የጋራ መግባባት በመፍጠር ምክረ ሃሳቦች ይቀረጹበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ለታሪካዊውና ታላቁ የሀገራዊ ምክክር በምትሰናዳበት በዚህ ወሳኝ ታሪካዊ ወቅት በዛሬው ዕለት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
ባስተላለፉት የጥሪ መልዕክት ነገ የሚጀመረው ውይይት ፍቱን የፖለቲካ መድረክ ብቻ ሳይሆን፤ የእኛን እና የመጪውን ትውልድ እጣ ፈንታና የወደፊት ተስፋ ሙሉ በሙሉ የሚወስን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ጭምር ነው ብለዋል።
ትናንት አባቶቻችንና እናቶቻችን በዓድዋ ለሀገር ነጻነት፣ ለሉዓላዊነትና ለክብር ሲሉ በደማቸውና በአጥንታቸው እንደተዋደቁላት ሁሉ፤ ዛሬም ኢትዮጵያ የታሪክ አደራ የሚሸከሙ የቁርጥ ቀን ልጆቿን ትፈልጋለች ነው ያሉት።
ዛሬ ሀገራችን የምትሻው ጠመንጃ ያነገቡ ሳይሆን በሀሳብ ብስለት፣ በእውነት፣ በዕውቀትና በጽናት ታጥቀው የተሰናዱ የሰላም ታጋዮችን ነው ሲሉም አስረድተዋል።
እኛ ዛሬም እንደ ትናንቱ በታላቅ የድል ዋዜማ ላይ እንገኛለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያና የሕዝቦቿ ማሸነፍ አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡
በሰለጠነ ንግግር፣ በሰላማዊ ውይይትና ሀገራዊ መግባባት የገጠሙንን ፈተናዎች በሙሉ አልፈን ወደ ብልጽግና በጋራ እንሻገራለን ነው ያሉት፡፡
በሀገራዊ ምክክር ሒደት ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ አለመግባባቶችን በሰለጠነ መንገድ ለመፍታትና ሀገራዊ መግባባት ለመፍጠር ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በአዲስ አበባ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄደው የምክክር ጉባኤ ከ4 ሺህ በላይ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ወኪሎች በአንድ ማዕከል ተገናኝተው የሀገርን ዕጣ ፈንታ የሚወስኑበት ትልቅ መድረክ ነው።