Fana: At a Speed of Life!

ቀይ ባሕርን ከኢትዮጵያ የነጠለው የሸፍጥ ፖለቲካ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ የራሷ የባሕር በር የነበራትና ለራሷም ሆነ ለቀጣናው ሀገራት ምቹ መደላድልን በመፍጠር የንግድ ሥርዓቷን ታሳልጥ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ያልተመረጠ እና ያልተወያየ መንግሥት በሰራው የፖለቲካ ሸፍጥና ሴራ እንዲሁም በውስጥ መከፋፈልና ስንፍና ሳቢያ የባሕር በር አልባ ሆና የጂኦግራፊ እስረኛ ሆነች፡፡

በዚህ እኩይ ታሪካዊ ክስተትም በአንድ ወቅት የባሕር በር እንዲሁም የባሕር ሃይል ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ ለቀይ ባሕር የቅርብ ሩቅ ለመሆን ተገደደች፡፡

ይህን የታሪክ ጠባሳ ለመሻር የለውጡ መንግሥት የጀመራቸው ሥራዎችም አሁን ላይ ድጋሚ ታሪክ እንዲሰራ የሚገፋፉና የቀይ ባሕርን ታሪካዊ የኢትዮጵያ ባለቤትነት የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ትላንት በተጀመረው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ላይ ያነሱት ሀሳብም ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር ባለቤትነቷን ለማስመለስ ያላት ቁርጠኝነት እየተጠናከረ መምጣቱን ያረጋገጠ ነው፡፡

ቀይ ባሕርን ያጣነው እኛ ስንጨቃጨቅ ጊዜ ጠብቀው ጣልቃ በመግባት መሻታችንን እንዳንከውን ባደረጉ ሃይሎች ነው ሲሉ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ÷ ለኢትዮጵያ ያላቸው ቂም በዘመናት ያልሻረላቸው ኮሽ ሲል ብቅ የሚሉ አድፋጮች አሉ ሲሉም አመልክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በዘመናት ጥቁር ጥላቸውን የሚጥሉባት እና የራሷን ልጆች በጥቅም ደልለው ከጉያዋ የሚመነትፉባት፤ መልሰውም ጠላት አድርገው የሚልኩባት ሃይሎች እጅግ ብዙ ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉትም÷ እነዚህ ጠላቶቿ ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ስትገነባ፣ ከተሞቿን ስታለማ እና ሌሎች ፕሮጀክቶችን ስትሰራ ሳይታዩ ልክ ስንጨቃጨቅ ግን ብር እና ባሩድ ያቀብላሉ፤ በሚዲያዎቻቸውም ፕሮፖጋንዳቸውን ይነዛሉ ነው ያሉት፡፡

ይሁን እንጂ ጠላቶቻችን የኢትዮጵያን ታሪክ በደንብ አገላብጠው አንብበው ማወቅ እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡ለምን ከተባለም ኢትዮጵያ ልጆቿ ሲጣሉ በሽምግልና፣ በመመካከር፣ በካሳ እና በይቅርታ ቂምን የመፍታት ባህል አላቸው ብለዋል፡፡

በመሆኑም በውስጣችን ያሉ ችግሮች እኛው ጀምረን እኛው የምንጨርሳቸው ብቻ አይደሉም ፤ የጠምባሮ አባቶች ከብት ሲገዛ የሌሉ አሞራዎች ከብት ሲታረድ በአካባቢው ያንዣብባሉ እንደሚሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ኮሽ ሲል ያደፈጡና የሚነቁ የዘመናት ያልተቋረጠ የጠላትነት ስሜት ያላቸው ሀገራት አሉ ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው÷ ነገር ግን በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ለሚያንዣብቡ አሞራዎች መልዕክት አለኝ፤ ከብቱን መርጠን የምንገዛ እኛ ነን፤ የቅርጫውን ባለቤት የምንወስን እኛ ነን፤ የተረፈንን የማንፈልገውን ካልሆነ በቀር የትኛውም አሞራ በጉልበት ከየትኛውም የቅርጫ መደብ ላይ አንዲት ኪሎ ስጋ መውሰድ እንደማይችል ላረጋግጥላቸው እፈልጋለሁ ነው ያሉት፡፡

ስንፈልግ ለማጋራት ዝግጁ ነን፤ ከፈቃዳችን ውጪ ግን ለሺህ ዓመታት የኖረች ኢትዮጵያን አሁን ባለው ፕሮፓጋንዳ ትዘናጋለች ፤ጥቅሟን አሳልፋ ትሰጣለች ብሎ ማሰብ ከንቱ ምኞት ነው ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

ይህ ታዲያ እንዲሁ ንግግር ብቻ አይደለም፤ በተግባር የተደገፈ በልጆቿ ምክክር እና ውይይት የውስጥ ችግሮቿን ፈታ ለነገዋ ብሩህ ትውልድ ሙሉ የሆነች ኢትዮጵያን የማስረከብ ተልእኮ እንጂ፡፡

ከ4 ሺህ በላይ ልጆቿን በአንድ ሰብስባ ልታማክር መድረክ የከፈተችው ኢትዮጵያ የነበሩባትን ችግሮች ፈትታ በሀይለ ቃል ተጀምሮ በሀይል ርምጃ የሚቋጨውን ፖለቲካዋን የምታርቅበት ፤ በሸፍጥ ፖለቲካ ያጣቸውን ቀይ ባሕርን ለማስመለስ ሥራዎቿን አጠናክራ የምትቀጥልበት ብሩሁ ጊዜ እነሆ ከፊቷ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ትመክራለች፣ ችግሮቿን ትፈታለች፣ ብሄራዊ ጥቅሟንም ፣ታስጠብቃለች ፤ ለዚህ ደግሞ ጊዜ ጠብቀው ጣልቃ በመግባት መሻታችንን እንዳንከውን የሚያደርጉ ሃይሎችን በጽኑ መጠበቅና መመከት ያስፈልጋል፡፡

በእመቤት ሲሳይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.