የቁጣን እሳት ማጥፋት…
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጉዳዮች በተመሰቃቀሉበትና ነገሮች መያዣ መጨበጫቸው በጠፋ ጊዜ ከችግሮች መውጫ መንገድ ጠቋሚና አስተማሪ ምክሮች ልምድ ካስተማራቸው ሰዎች ድንገት ይሰነዘሩና የተስፋ ብርሃን ይፈነጥቃሉ፡፡
በሀገራችን ታሪክ ወሳኝ ምዕራፍ በሆነ የሰላም እና የመግባባት ፍለጋ ከምንም በላይ በሆነበት በዚህ ታሪካዊ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር መድረክ መክፈቻ ላይ ከደቡብ ኦሞ ዞን ከሐመር ወረዳ የካራ ብሔረሰብን የወከለችው ሙዶ አኮ በሀገር ፊት ቆመች።
እጆቿ በፍርሃት ቢንቀጠቀጡም ልቧ ግን በፍጹም ተስፋ ተሞልቶ ነበር። የሀገራችንን ፈተናዎች ከሩቅ ቆመው ሲመለከቱ፣ በዝምታ የሚወዷቸውን ሲቀብሩና እምባቸውን ሲያዘሩ ለኖሩት ለበርካታ ሴቶች ጭምር ድምጽ ሆና ተናገረች።
የእሷ በታላቁ መድረክ መገኘት ብቻውን የበርካታ ማሕበረሰቦችን ጥቅም ላይ ያልዋለ አቅም የሚያሳይ ቢሆንም አዳራሹን ያናወጠው ግን ያስተላለፈችው መልዕክት ነበር።
የእሷ ንግግር አሁን ያሉትን ሀገራዊ ፈተናዎች በቀጥታ የሚፈታ ጥልቅ እውነት ይዟል፤ ሀገርን ሊያጠፋት በሚችለው በቁጣ እሳት የጋራ ቤት ለመገንባት መሞከር ምን ያህል ውድመት እንደሆነ ያስታወሰ ነው፡፡
“እሳት ቤት ቢገነባ ኖሮ ኢትዮጵያ ከዘመናት በፊት በተገነባች ነበር” ስትል ሃሳቧን ገልጻለች። በዚህም ቤት አሊያም ሀገር ሊገነባ የሚችለው እጆች ለስራ ሲተባበሩና ልቦች እርስ በርስ ሲደማመጡ ብቻ እንደሆነ አረጋግጣለች።
ለተወካዮቹና ለመላው ሕዝብ ያቀረበችው ጥሪም የገዘፈና ሃላፊነትን የሚያስታውስ ነው፡፡ ይዘነው የመጣነውን የቆየ ቁጣና የታሪክ ቋጠሮ ይዘን መመለስ የለብንም፤ አብረን ተቀምጠን እንመካከርና ቋጠሮዎቻችንን መፍታት አለብን የሚል መልዕክትን ያስተጋባል፡፡
ንግግሯ የያዘው እውነት ዛሬ ኢትዮጵያ ለሕመሞቿ የምትፈልገውንና ትክክለኛውን መድኃኒት የተሸከመ አስተሳሰብ ነው።
ሀገር በጩኸትና በተከፋፈለ ማንነት በተወጠረችበት በዚህ ወቅት የደቡብ ኦሞዋ ተወላጅ ንግግር የጥበብ መስታወት ሆኗል።
ይህም በየአካባቢው ያሉ ቱባ ባሕሎችና ሀገር በቀል እውቀቶች የሰላም ቁልፍ መሆናቸውን ያስገነዝባል፤ ልዩነቶች የግጭት መንስዔ ሳይሆን የውበት መገኛ መሆናቸውን ያረጋግጣል።
እውነተኛ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር፣ “ማን ያሸንፋል?” ከሚለው የአንድ ወገን ፍላጎት በመውጣት የጋራ ቤት የሆነችውን ኢትዮጵያን እንዴት አሸናፊ ማድረግ እንደሚቻል መምከር ይበጃል የሚለውን ሃሳብ አጽንኦት የሚሰጥም ነው፡፡
የሀገራዊ ምክክሩን መድረክ እንደ ፍላጎቶች መጠየቂያ ብቻ ሳይሆን የተስፋ፣ የመግባባትና የአንድነት እድል አድርጎ በመጠቀም የቁጣን እሳት ማጥፋት፣ ለስራ መተባበር፣ ልብ ለልብ መደማመጥና ያለፈውን ታሪክ ቋጠሮ በጋራ መፍታት ያስፈልጋል፡፡
በምህረት ደምሴ