Fana: At a Speed of Life!

ብሔራዊ ጥቅማችንን አሳልፈን ላለመስጠት የማያግባቡንን ጉዳዮች በምክክር መፍታት አለብን – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 9፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈን በመስጠት የታሪክ እንክርዳድ ላለመሆን የማያግባቡንን ጉዳዮች በምክክር መፍታት አለብን አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንትናው ዕለት በተካሄደው የሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ እንዳሉት፥ ብሔራዊ ጥቅማችንን ሊነጥቁን የሚያንዣብቡ ኃይሎችን ማራቅ ይገባል፡፡
በኢትዮጵያውያን መካከል አለመግባባቶች በተፈጠሩና ግጭቶች በተቀሰቀሱ ቁጥር በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት ሰላሟን ሊያውኩና እድሎቿን ሊነጥቁ ያደፈጡ የዘመናት ጠላቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለሺህ ዘመናት ጠብቃ ያቆየችውንና ያስተዳደረችውን ቀይ ባህር የተነጠቀችው በዚሁ የውስጥ አለመግባባት እንጂ ጥቅሟንና መሻቷን ማስቆም የሚችል ኃይል ኖሮ አይደለም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከራሷ አልፋ ለከባቢው መጠቀሚያ ያኖረችውን ቀይ ባሕር ያጣችው በውስጥ ስንፍና እና አለመመካከር መሆኑን ገልጸው፥ ሀገር ስንገነባና ስናለማ ያልነበሩ ኃይሎች ክፍተታችንን ተጠቅመው ብሔራዊ ጥቅማችንን ሊነጥቁን ያንዣብባሉ ነው ያሉት፡፡
የእኛን ስንፍናና ጊዜን እየጠበቁ ጥቅሞቻችንን እንዳናስጠብቅ የሚያደርጉንን ኃይሎች በማራቅ የሀገርን ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
የውስጥ አለመግባባቶችን በግልጽ በመመካከርና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት ከታሪክ ተወቃሽነት መዳን አለብን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ለተተኪ ትውልድም የተሻለች ሀገር ማቆየት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
እኛ ስንፈልግ ለማጋራት ዝግጁ ነን፤ ነገር ግን ከፍቃዳችን ውጪ ለሺህ ዓመታት የጸናችና በቀላሉ በማይበጠስ ገመድ የተሰናሰለች ኢትዮጵያ አሁን ባለው ፕሮፓጋንዳ ተዘናግታ ጥቅሟን አሳልፋ ትሰጣለች ብሎ መገመት ከንቱ ምኞት ነው ብለዋል፡፡
ከወዲሁ የኢትዮጵያን ታሪክ በትክክለኛ መንገድ ተገንዝባችሁ ቀልባችሁን በመመለስ ለጋራ ጥቅም በጋራ እንስራ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በምሕረት ደምሴ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.