Fana: At a Speed of Life!

የሀገራዊ ምክክር አዲስ ምዕራፍ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 14፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ)የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከተወካዮች መረጣና ከአጀንዳ ማሰባሰብ ሒደት በኋላ ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ታሪካዊ የምክክር ጉባዔውን በአዲስ አበባ በይፋ መጀመሩ ይታወሳል።

ጉባዔው የመጀመሪያዎቹን አራት ቀናት በቅድመ ምክክር፣ በትውውቅና በሥነ ሥርዓት ደንቦች ግንዛቤ ላይ ካሳለፈ በኋላ ትናንት ሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ወደ ወሳኙ ምዕራፍ ተሸጋግሯል።

በዚህም ከ4 ሺህ በላይ ተሳታፊዎችን ያቀፈው ጉባዔ ለይቶ ባዘጋጃቸው 8 መሠረታዊ ብሔራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ በየዘርፉ በንዑስ ቡድኖች ተከፋፍሎ ጥልቅና መዋቅራዊ ውይይት መካሄድ ተጀምሯል፡፡

ይህ በንዑስ ቡድን የመወያየት መዋቅር መደበኛ የውይይት መድረክ ከመሆን ባለፈ ሀገር የገጠሟትን ውስብስብና ስር የሰደዱ የፖለቲካ፣ የታሪክና የማንነት ቅራኔዎችን መስመር የሚያስይዝ ፍቱን ስልት መሆኑን በተጨባጭ እያሳየ ይገኛል።

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር መሐሙድ ድሪር በሰጡት መግለጫ እንዳሉት÷ የምክክር ጉባዔው ሒደት ሃሳብን በነጻነት ለመለዋወጥ እንዲያመች ተደርጎ በጥንቃቄ ተደራጅቷል።

በዚህም ስምንቱን ብሔራዊ አጀንዳዎች መሠረት በማድረግ ለእያንዳንዱ አጀንዳ 500 ተመካካሪዎችን የያዙ ስምንት ዋና ዋና የሥራ ቡድኖች ተቋቁመዋል።

እነዚህ ቡድኖች እያንዳንዳቸው በውስጣቸው 50 ተሳታፊዎችን የያዙ ሲሆን÷ በአጠቃላይ 80 ንዑስ ቡድኖች በትይዩ ውይይት እያካሄዱ ይገኛሉ።

በተጨማሪም እያንዳንዱ ንዑስ ቡድን 10 አባላት ብቻ የሚገኙባቸው አምስት ጥቃቅን ቡድኖችን አካትቷል፡፡

በዚህም መሰረት በንዑስ ቡድኖቹ ውስጥ ከተለያዩ ክልሎች የመጡ ዜጎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ሲቪክ ማኅበራት እና ምሁራን በጋራ ተቀምጠው እየመከሩ ነው።

ይህ ስልታዊ መዋቅር በትልልቅ መድረኮች የሚታየውን “ጥቂቶች ተናግረው ብዙዎች የሚሰሙበትን” የተለመደ አሠራር የሚሰብር ነው።

በተጨማሪም የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን ድምፅ በአንድ ማዕድ ላይ ማምጣቱ የሚቀርቡት የመፍትሔ ሃሳቦች ሁሉንም ወገን ያማከሉ እንዲሆኑ ያደርጋል።

የውይይቱን ሒደት በገለልተኝነት፣ በትሕትናና በትዕግሥት እንዲመሩ የተመረጡ 160 አመካካሪዎች እና 256 የቃለ ጉባዔ ጸሐፊዎች የተመደቡ ሲሆን÷ እነዚህ ባለሙያዎች ውይይቱ ከስሜታዊነት ወጥቶ ወደ ገንቢ የጋራ መግባባት እንዲያመራ መንገድ የማሳየት ትልቅ ሚና የሚጫወቱ ይሆናል።

ውይይቶቹ የሚካሄዱት በዘፈቀደ ሳይሆን ባለፉት ዓመታት ከሕዝብ በቀጥታ በተሰበሰቡና መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን በሚጠይቁ አጀንዳዎች ላይ ነው፤ንዑስ ቡድኖቹ የሚያመጧቸው ምክረ-ሃሳቦች የችግሩን ስር የሚነኩ እንጂ ቅርንጫፍ ላይ የሚንጠለጠሉ አይሆኑም።

ትናንት በይፋ የተጀመረው የንዑስ ቡድኖች ጥልቅ ውይይት ተሳታፊዎች ለሀገር መዳን ፍቱን መድኃኒት የሚሆን የጋራ መግባቢያ ሃሳብ ይዘው እንዲቀርቡ ትልቅ ዕድል የፈጠረ የሀገራዊ ምክክሩ ቁልፍ ምዕራፍ ነው።

በሶስና አለማየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.