ኅብር፡ የኢትዮጵያ ውበትና የጥንካሬ መሠረት
አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በታሪክ ማዕበል ውስጥ ጸንታ እስከዛሬ የዘለቀችው ኢትዮጵያ የማንነቷ ውበትና የጽናቷ ምስጢር በብዝኃነቷ ውስጥ ያለው ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ነው።
የኢትዮጵያ ታሪክ ገጾችን ወደኋላ ተመልሰን ስንመለከት ኢትዮጵያውያን ሉዓላዊነታቸውንና ነጻነታቸውን ለማስከበር በወሳኝ ወቅቶች በአንድነት በመቆም ያሳዩት ቆራጥኝነት፣ በብዝኃነታቸው ውስጥ የተገነባውን የኅብር ኃይል ያሳያል።
በዓድዋ ተራሮች ላይ የፈነጠቀው ታላቅ ድልም የዚሁ አንድነት ውጤት ሲሆን፤ ከተለያዩ የሀገሪቱ ማዕዘናት የተመሙ አባቶቻችን በአንድ የሀገር ፍቅር ስር ተሰልፈው የድል ታሪክ ጽፈዋል።
ይህም ልዩነት ለአንድነት እንቅፋት ሳይሆን በጋራ ዓላማ ሲመራ የጥንካሬ ምንጭ ሊሆን እንደሚችል የሚያስተምር ታሪካዊ ምስክር ነው።
የኢትዮጵያ ጥንካሬ ምልክት የሆነው ብዝኃነቷም ሀገሪቱ በአንድ ቀለም የተሳለች ሳትሆን፤ በበርካታ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ እምነቶችና ማንነቶች የተዋበች ሀገር መሆኗን ያመለክታል።
እነዚህ ልዩነቶች በአንድ የሀገር ርዕይ ሲገናኙ ለጋራ የልማት ግብና ዓላማ የሚያስፈልገውን የጋራ ኃይል ይፈጥራሉ።
ኅብር በተለያዩ ቋንቋዎች፣ እምነቶችና ባህሎች የተሰባሰበችውን ኢትዮጵያን የሚያስውብ ብቻ ሳይሆን፤ የጋራ ሀገራዊ ጥቅምን በማስቀደም የልማት ዓላማዎችን ለማሳካት የሚያስችል ዋነኛ መሠረት ነው።
የታሪክና የፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪው ኢብራሂም ሙሉሸዋ እንደሚገልጹት፣ አንድነት ማለት ልዩነትን መካድ ሳይሆን፤ ልዩነቶችን በመቀበል በጋራ ዓላማ ላይ መቆም እንደሆነ እና የሀገር ጥንካሬም የሚገለጠው እንደ ሀገር አንድ ሆኖ በመቆም መሆኑን ያስረዳሉ።
በእሳቸው ዕይታ፤ አሁን ያለው ትውልድ ለሀገራዊ ጥቅሙና ለኢኮኖሚ እድገቱ የሚጠበቅበትን መስዋዕትነት በመክፈል ወደ አንድነትና መከባበር ሲመጣ ተዓምራዊ ለውጥ ማስመዝገብ ይቻላል፡፡
የዓለም ታሪክም ብዝኃነትን በመቀበል በጋራ ሀገራዊ ጥቅም ላይ ተመሥርተው ዕድገትን ያስመዘገቡ ሀገራትን ያሳያል። እንደ ቻይናና ሕንድ ያሉ ሀገራትም በብዙ ማንነቶች መካከል የጋራ ብሔራዊ ጥቅምን ማስቀደምና የልማት ዓላማን ማዕከል ማድረግ ከቻሉ ሀገራት መካከል ይጠቀሳሉ።
የፖለቲካ ጉዳዮች ተመራማሪው ጌትዬ ትርፌ (ዶ/ር) እንደሚሉት፣ ብዝኃነትና ታሪክን ለሀገር አንድነትና ለትውልድ ግንባታ ማዋል ከአሁኑ ትውልድ የሚጠበቅ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ነው።
እያንዳንዱን ባህል፣ ቋንቋና ማንነት በኢትዮጵያ ጥላ ሥር በማስተናገድና በማጎልበት፣ የተለያዩ ማንነቶችን በጋራ የልማትና የብሔራዊ ጥቅም እሳቤ ዙሪያ ማሰባሰብ እንደሚገባም ያሳስባሉ።
ኅብር የሚጠነክረው በመከባበር፣ በመቻቻል፣ በመረዳዳትና ለጋራ ጥቅም በመቆም ነው። ከማንኛውም ልዩነት በላይ የሚያገናኙንን የጋራ እሴቶች ማጠናከር ሲቻል፣ ብዝኃነት የመከፋፈያ ምክንያት ሳይሆን የጋራ ኃይል ምንጭ ይሆናል።
ኅብርና ልዩነት የኢትዮጵያ ውበት፣ አንድነት ደግሞ የጽናቷ መሠረት ናቸው። እነዚህን እሴቶች መጠበቅ፣ ማጎልበትና ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ የእያንዳንዳችን ሀገራዊ ኃላፊነት ነው።
በዮናስ ጌትነት