የሐይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ ሚና አላቸው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የሐይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ ወሳኝ ሚና አላቸው አለ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ፡፡
የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ‘ብዝሃነትና የሠላም እሴታችን ለዘላቂ ሠላማችን’ በሚል መሪ ኃሳብ ከሐይማኖት ተቋማት መሪዎችና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር እየመከረ ነው፡፡
የቢሮው ም/ኃላፊ እንዳለ ወ/አማኑኤል በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የሐይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ለዘላቂ ሰላም ግንባታ አይተኬ ሚና አላቸው።
በሰላም ዙሪያ የሚደረገው ውይይት ከወትሮው የተለየና ትኩረት የሚሻ መሆኑን አንስተው÷ የሕዝቡን አብሮነት ለማጠናከር እና የሰላም እሴቱን ለማስጠበቅ ውይይቱ ስንቅ ይሆናል ብለዋል፡፡
የሐይማኖት አባቶችና የባህል ሽማግሌዎች የማሕበረሰቡን የሰላም ዋስትና እንዲሁም የክልሉን ልማት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ ጠቅሰዋል፡፡
ከክልሉ ጸጥታ መዋቅር ጋር በመተባበር ጠንካራ የሰላም ድልድይ ለመገንባት መሰል የውይይት መድረኮች አስፈላጊ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ሰላም ከሌለ ሐይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶችን በሚገባ ማስቀጠል እንደማይቻል ገልጸው ÷ ሰላም በሕግና በሃይል ብቻ የሚጠበቅ ቁስ እንዳልሆነም ተናግረዋል፡፡
ክልሉ የተለያዩ ባሕል፣ ቋንቋ፣ ሐይማኖት እና ማንነት ያላቸው በርካታ ሕዝቦች በሰላምና በፍቅር የሚኖሩበት የብዝኃነት መገለጫ መሆኑን አውስተዋል፡፡
ይህንን የመደመር ማሳያ ጠብቆ በማቆየት ቀጣይ የአብሮነት ጉዞን ለማጠናከርም በቅንጅት መስራት እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡
በመድረኩ ጥልቅ ማሕበራዊ ስብራትን በተግባር የመጠገን የቆየ ጥበብ ያላቸው የሐይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች ተሳትፈዋል፡፡
በተካልኝ ኃይሉ