Fana: At a Speed of Life!

አረጋውያንን የመንከባከብ ባህልን የሚያጸናው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 20፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ክረምቱ ሲያስገመግም እና የሰማይ መስኮቶች ሲከፈቱ ታላቅ ተስፋን የሚፈነጥቀውን ያህል በተጎሳቆሉ ጎጆዎች ለሚኖሩቱ ደግሞ ስጋትን ያዋልዳል።

ጠንካራ ቆርቆሮ ላይ የሚያርፈው የዝናብ ጠብታ ድምፅ ለብዙዎች እረፍት የሚሰጥ ሆኖ ቢሰማም፣ በፈራረሱ ቤቶች ውስጥ ለሚኖሩ በርካቶች ግን ዝናብ ትልቅ ስጋት እና ጭንቀት ነው።

የሚያንጠባጥብ ጣራ ጭቃማ ወለል እና በግድግዳዎች ስንጥቅ የሚገባው ብርድ ለወራት የሚዘልቅ ስጋትና መከራን ያመጣል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የበጎ ፈቃደኞች የልማት እንቅስቃሴ በገንዘብ፣ በጉልበት እና ጊዜ መስዕዋትነት የክረምቱን ወቅት ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የመታደስ እና የክብር ማድረግ ችሏል።

በየዓመቱ ትምህርት ቤቶች ለእረፍት ሲዘጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በብሔራዊ የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመሳተፍ ወደ ማስተባበሪያ ማዕከላት ይመጣሉ።

በትኩስ የወጣትነት መንፈስ ተሞልተው የወገናቸውን ኑሮ በልዩ ልዩ ዘርፎች ለመቀየር ይረባረባሉ፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ክልል ከተሞች ያሉ ሰፈሮችን ገጽታ በትብብር ይለውጣሉ።

በአዲስ አበባ ብቻ በየክረምቱ በ90 ቀናት ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ያረጁ ቤቶችን ለመጠገን እቅድ ተይዞ እየተሰራ ሲሆን፤ ይህም በቅርብ ዓመታት በወጣቶች እጅ የታደሱትን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ የአረጋውያን መኖሪያዎች ቁጥር የበለጠ ያጎለብተዋል።

ስራው በጉልበት ረገድ ፈታኝ ቢሆንም፣ በስፍራው ያለው የበጎ ፈቃደኝነት መንፈስ ግን የማይበገር ነው። ወጣቶች ዝናብ ማስገባት የጀመሩትን ያረጁና የዛጉ ቆርቆሮዎችን በማንሳት ስራቸውን ይጀምራሉ።

አዲሱንና ውሃ የማያስገባውን ቆርቆሮ በጣራው ላይ ሲመቱ፣ ሌሎች ደግሞ ሲሚንቶ በማቡካት የተናዱትን ግድግዳዎች ያጠናክራሉ።

ቀደም ሲል በዝናብ ወቅት የአፈር ወለላቸው ጭቃ ይሆን የነበሩ ቤቶች፣ የበጎ ፈቃደኞቹ አበርክቶ ለአረጋውያኑ ደረቅ፣ ንጹህ እና የተመቻቸ ወለል ያዘጋጅላቸዋል።

ማደሪያና ማብሰያ ቦታዎች ተለይተው፣ በቂ ብርሃን የሚያስገቡ ሆነው ይገነባሉ በገንዘብና እቃ ማሰባሰብ ስራዎች የታደሱት ቤቶች በአስፈላጊ ቁሳቁስ ይሟላሉ በመኖሪያ አካባቢያቸው ዙሪያ ያሉት ቆሻሻዎች ይጸዳሉ፣ የፍሳሽ መስመሮችን ይቆፍራሉ አረጋውያንና አቅመ ደካማ ወገኖች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ እና በምቾት እንዲኖሩ ያደርጋሉ።

ከአዲስ ቤትና አኗኗር ባሻገር ከበጎ ፈቃደኞች ሰብአዊ ፍቅርንና እንክብካቤን ያገኛሉ።

ይህን ሀገር አቀፍ እንቅስቃሴ ልዩ የሚያደርገው በወጣቶች እና በአረጋውያን መካከል የሚፈጠረው ጥልቅ ፍቅርና ትስስር ልብ የሚያሞቅ መሆኑ ነው።

ወጣቶቹ ጉልበታቸውን እና እውቀታቸውን ሲሰጡ፣ አረጋውያኑ ደግሞ ምርቃታቸውን፣ ምክራቸውን እና ደስታቸውን ያካፍላሉ።

በሚሊየን የሚቆጠሩ ወጣቶች በየክረምቱ ከከተማ አስተዳደሮች እና ከለጋስ ማህበረሰብ ጋር በመተባበር የሚያደርጉት ይህ በጎ ተግባር ያዘመሙ ጎጆዎችን ከመጠገን በላይ የኢትዮጵያውያንን የቆየ አረጋውያንን የማክበርና የመንከባከብ ባህል የሚያጸና ለአቅመ ደካሞችም የመኖር ተስፋን የሚያለመልም ነው።

በምሕረት ደምሴ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.