Fana: At a Speed of Life!

የሀገር ሉዓላዊነት ሃያል ጋሻ

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 18፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት እና ክብር የሚለካው በድንበሯ ጥንካሬና በሕዝቦቿ ሰላም ነው።

ይህንን ሰላምና ክብር ለማስጠበቅ ደግሞ ሌት ከቀን ሕይወቱን ሳይሰስት በቁርጠኝነት የሚሰጥ፣ በታሪክ ውሽንፍሮች ውስጥ አልፎ የጸና ጠንካራ ተቋም ያስፈልጋል።

የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት በትክክልም የዚህ እውነት ነጸብራቅ ነው።

ተቋሙ የረጅም ዘመናት ወታደራዊ ታሪክና የጀግንነት አሻራን ከዘመናዊው ዓለም ወታደራዊ ሳይንስ እና የቴክኖሎጂ ምጥቀት ጋር አቀናጅቶ የያዘ የሀገር ሉዓላዊነት ኃያል ጋሻ ነው።

ይህ ታላቅ ሠራዊት የአንድ ወገን ወይም የአንድ ቡድን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ የብዝሃነቷ መገለጫ በሆነው ሕገ መንግሥት ጥላ ሥር የኢትዮጵያን ሕዝቦች አንድነት ባንጸባረቀ መልኩ የተዋቀረ የሕዝብ ልጅ ነው።

የሠራዊቱ የዕዝ ሰንሰለት በሕግና በዲሲፕሊን የተገነባ ሲሆን ÷ ጥንካሬው የሚመነጨውም በተቀናጀው የክፍሎቹ አወቃቀር ነው።

ሰፊውን የሰው ኃይል የያዘው የምድር ኃይል በተለያዩ የሀገሪቱ አቅጣጫዎች ማለትም በምሥራቅ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን፣ ደቡብ እና መካከለኛ ዕዞች ተከፋፍሎ ድንበርን በአስተማማኝ ሁኔታ ይጠብቃል።

በሰማይ ደግሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል በዘመናዊ ተዋጊ ጄቶችና በሄሊኮፕተሮች የታገዘ የአየር ክልል ዘብ ሆኖ ቆሟል። ዘመን ሲቀየር የውጊያ ስልቶችም አብረው ይቀየራሉ።

ይህንን የተረዳው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በቅርቡ ባደረጋቸው ሰፋ ያሉ የሪፎርም ሥራዎች ራሱን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ አደራጅቷል።

ከዚህም በላይ በአሁኑ ወቅት እየተበራከተ የመጣውን የሳይበር ጥቃት ለመከላከል በዘርፉ የመከላከል አቅሙን ያጠናከረ ሲሆን÷ በሀገር ውስጥ የሚገኙ የመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪዎችም ለሰራዊቱ የሚሆኑ የጦር መሣሪያዎችን፣ ጥይቶችንና ወታደራዊ ተሽከርካሪዎችን በማምረትና በመጠገን ረገድ ተቋሙ በራስ የመተማመን አቅሙን እንዲያሳድግ አድርገውታል።

የመደመር መንግሥት በተለይም የዘመኑን ውጊያ ስልት አጢኖ የሚረዳ የሰለጠነ የሰው ሃይል እንዲሁም ውጊያ ጨራሽ የሆኑ ሰው አልባ አውሮፕላኖችና ሌሎች ተዋጊ ጀቶች መታጠቅ ላይ በትኩረት እየሰራ ነው፡፡ለዚህም ለሲቪልና ወታደራዊ አገልግሎት የሚውሉ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን የሚያመርተውን ስካይ ዊን ኤሮኖቲክስ ኢንዱስትሪ መጥቀስ ይቻላል፡፡

መከላከያ ሠራዊት የጠላት እንቅስቃሴዎችን በቅጽበት ለመከታተል፣ ጥናት ለማድረግ እና ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የተለያዩ የውጊያ ቴክኖሎጂዎችንም እየታጠቀ ነው፡፡

በሀገር ላይ ጥቃት የሚፈጸም ከሆነ ጥቃቱን በአጭር ጊዜ ለመቀልበስና በትንሽ ኪሳራ ከመጨረስ ባለፈ ግጭትን የማስቀረት አቅሙ ያለው ሰራዊት የመገንባቱ ሒደትም ተጠናክሯል፡፡

በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዝና ከሀገር ድንበር አልፎ በዓለም አቀፍ መድረኮችም በጉልህ ስሙ ይነሳል።

በተባበሩት መንግሥታትና በአፍሪካ ሕብረት ጥላ ሥር በኮሪያ፣ ኮንጎ፣ ሩዋንዳ፣ ላይቤሪያ እና ሶማሊያ የተከናወኑት ስኬታማ የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች የሰራዊቱን ወታደራዊ ሥነ ምግባር እና ሰብአዊነት ለዓለም ያስመሰከሩ ናቸው።

የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በትናንትናው ታሪካዊ ጀግንነት ላይ ቆሞ የነገዋን ዘመናዊትና የበለጸገች ኢትዮጵያን ሰላም በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ ዛሬም ታጥቆ እና ተደራጅቶ በተጠንቀቅ ቆሟል፡፡

በእመቤት ሲሳይ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.