Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያን የጋራ እሴቶች በማጠናከር ዘላቂ ህብረ ብሔራዊ አንድነት እየተገነባ ነው – ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን የጋራ እሴቶች በማጠናከር ዘላቂ ህብረ ብሔራዊ አንድነት እየገነባ ነው አሉ የፓርቲው የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)፡፡

የፓርቲው የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ በ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምና በ2019 በጀት ዓመት ዋና ዋና ዕቅዶች ላይ የሚመክር መድረክ በባሌ ሮቤ ከተማ እያካሄደ ነው፡፡

ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፥ ዘርፉ የፓርቲውን ፖሊሲዎች፣ ራዕይ እና የልማት አጀንዳዎች እንዲሁም ስኬቶች ለሕዝብ በማድረስ ለ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

ምርጫው የሕዝብ ፍቃድ፣ የተቋም ግንባታና የትውልድ ኃላፊነት የተረጋገጠበት ታሪካዊ ምዕራፍ መሆኑን አውስተዋል፡፡

ፓርቲው ሁሉንም የተግባቦት መንገዶች በመጠቀም የጋራ እሴቶችን በማጠናከር ዘላቂ ህብረ ብሔራዊ አንድነትን እየገነባን ነው ያሉት ኃላፊው፥ የሕዝብ ተሳትፎን በማስፋት በልማት፣ በሰላምና በብሔራዊ ግንባታ ጉልህ ውጤቶች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

ዘርፉ በቀጣይም የሀገራዊ ግቦችን ስኬት የሚያግዝ የኮሙኒኬሽን አቅም በመገንባት እንደሚሰራ ጠቁመው፥ ኢትዮጵያን በማየት፣ በመረዳትና በማስተዋወቅ የጋራ ሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልፅግና እናረጋግጣለን ነው ያሉት፡፡

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የግምገማ መድረክ ላይ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸምን በመገምገም የ2019 በጀት ዓመት የሥራ አቅጣጫዎች እንደሚቀመጡ የፓርቲው መረጃ ያመለክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.