የምስራቅ አፍሪካ ቀጣና የሕጻናት ጥበቃ ዓውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ሐምሌ 21፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የምስራቅ አፍሪካ የፖሊስ አዛዦች ህብረት ድርጅት አባል ሀገራት፣ የኢንተርፖል የምስራቅ አፍሪካ ቀጣናዊ ቢሮ እና አጋር ድርጅቶች ባለሙያዎች የተሳተፉበት ቀጣናዊ የሕጻናት ጥበቃ ዓውደ ጥናት በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የአስተዳደርና ልማት ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ም/ኮሚሽነር ጀነራል ነብዩ ዳኜ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ የህፃናትን ደህንነት መጠበቅ የሁሉም ማህበረሰብ ኃላፊነት ነው፡፡
በቀጣናው ያሉ ህፃናት ከድህነት፣ ከግጭት፣ ከመፈናቀል፣ ከቤተሰብ መበታተን እና በተራቀቁ የተደራጁ ወንጀሎች ከፍተኛ አደጋዎች ተጋርጠውባቸዋል ብለዋል።
አሁን ላይ እነዚህ ተግዳሮቶች ከሀገርና ድንበር የዘለሉ አሳሳቢ ችግሮች እየሆኑ መምጣታቸውንና በተለይም ወንጀለኞች ቴክኖሎጂዎችንና በሕግ እና ተቋማዊ ሥርዓቶች ላይ ያሉ ክፍተቶችን በመጠቀም አሁንም የወንጀል ድርጊቱን እየፈፀሙ እንደሚገኙ ጠቅሰዋል፡፡
በመሆኑም ድርጊቱን ለመከላከል የቀጣናው የፀጥታ አካላት ምላሽ የተናጠል ሳይሆን የተቀናጀ፣ መረጃን መሰረት ያደረገ እና የጋራ ትብብርን ያጠናከረ ሊሆን እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
በናይሮቢ የምስራቅ አፍሪካ ኢንተርፖል ቢሮ ስፔሻላይዝድ ኦፊሰር አቶ መስፍን አበበ በበኩላቸው÷ በቀጣናው ሀገራት የሚገኙ ህፃናት ከወንጀል ስጋቶች የተነሳ ከፍተኛ ተጋላጭነት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል ::
በተለይም የወንጀል አይነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀያየሩ፣ ይበልጥ እየተወሳሰቡና ድንበር ተሻጋሪ እየሆኑ መምጣታቸውን አብራርተዋል፡፡
ዐውደ ጥናቱ የህፃናት ጥበቃ ረቂቅ ማዕቀፍን ለመገምገም፣ ልምዶችን ለመካፈል እና በሥራ ላይ የሚያጋጥሙ የዕለት ተዕለት ተግዳሮቶችን ለመቅረፍ ልዩ ዕድል ከመስጠቱም ባሻገር ፖሊሲዎችን ለመቅረጽ እጅግ ጠቃሚ እንደሚሆን ጠቁመዋል።