Fana: At a Speed of Life!

በአዲስ አበባና አከባቢው ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ማንኛውንም ድሮን ለማብረር ፈቃድ አይሰጥም – የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ እና አከባቢው ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ ማንኛውንም ድሮን ለማብረር ፍቃድ አይሰጥም አለ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት የድሮንና ሌሎች ተመሳሳይ በራሪ አካላት አጠቃቀምን በተመለከተ ይፋ ባደረገው ማሳሰቢያ፤ ከዛሬ ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ በአዲስ አበባ እና አከባቢው ማንኛውንም አይነት ድሮን ለማብረር ፍቃድ አይሰጥም፡፡
አገልግሎት መሥሪያ ቤቱ እንዳመለከተው፤ እንደ ወትሮው ሁሉ በአዲስ አበባና አካባቢው የሚንቀሳቀሱ ድሮኖችንና ሌሎች ተመሳሳይ በራሪ አካላትን የሚቆጣጠር የተቀናጀ የጸረ-ድሮን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ክትትልና ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል፡፡
የተሰጠውን ማሰሰቢያ በመጣስ የሚነሱ እንዲሁም በየትኛውም አካባቢና ከፍታ የሚበሩ ድሮኖችን በመለየት፣ በመጥለፍ እና ወደ አስፈላጊው ቦታ በማሳረፍ እንዲሁም የአብራሪዎቹን ትክክለኛ መገኛ ቦታ በመለየትና በቁጥጥር ስር በማዋል ሕጋዊ እርምጃ ይወሰዳል፡፡
ከዚህ ቀደም በሥራ ምክንያት ድሮኖች መጠቀም የሚፈልጉ አካላት የበረራውን ዓላማ፣ የሚበርበትን ቦታ፣ የድሮኑን አይነት እና የሞዴል ቁጥር በመጥቀስ አስቀድመው ለብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በመጠየቅ እና ፈቃድ በማግኘት ሲጠቀሙ እንደነበር ያስታወስው ማሳሰቢያው፤ ተቋሙ በአዋጅ ቁጥር 1276/2014 በተሰጠው ስልጣን መሠረት የመሪዎችን፣ የቁልፍ መሠረተ-ልማቶችን እና ብሔራዊ ኩነቶችን ደኅንነት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን የማስጠበቅ ኃላፊነቱን ለመወጣት ላልተወሰነ ጊዜ ፍቃድ መስጠቱንና የበረራ ክልከላውን ተግባራዊ ማድረጉን አስታውቋል፡፡
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋሉ የመጡ ድሮኖች እና መሰል ቴክኖሎጂ ወለድ መሣሪያዎች የሚፈጥሯቸውን የብሔራዊ ደኅንነት ስጋቶችን ለመከላከል የሚያስችሉ የረቀቁ ቴክኖሎጂዎችን መታጠቁንና ብቁ የሰው ኃይል ማፍራቱን የጠቆመው መረጃው፤ ማሳሰቢውያውን ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ለማስፈጸም በቂ ዝግጅት እንዳለው አመልክቷል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.