Fana: At a Speed of Life!

የኢትዮጵያ ቀጣናዊ አብሪ ኮከብነት ሚና፡ ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ርዕይ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 20፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ እያሳየች ያለው ፈጣን ዕድገት እና የቀጣናውን ሀገራት በጋራ የማልማት ጽኑ ቁርጠኝነት አፍሪካ በራሷ አቅም ተባብራ ማደግ የምትችልበትን አዲስ ምዕራፍ እየቀረጸ ይገኛል።

በዚህ ረገድ ዛሬ እንዲሁም በዚህ ሳምንት የተከናወኑ ሁለት ታላላቅ ስትራቴጂካዊ የኃይል እና የኢኮኖሚ ትስስሮች የኢትዮጵያን ቀጣናዊ መሪነትነና አብሪ ኮከብነት የሚያረጋግጡ ድንቅ ማሳያዎች ናቸው።

በዛሬው ዕለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኬንያ የላሙ ነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባታ ማስጀመሪያ ሥነ ሥርዓት ላይ ተሳትፈዋል፤ ይህም የኢትዮጵያ የቀጣናውን የስትራቴጂካዊ አጋርነት ማሳያ ነው።

በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የላሙ የነዳጅ ማጣሪያ ፕሮጀክት ግንባታ የአፍሪካን የኢንዱስትሪ አቅም ለማሳደግ፣ መጠነ ሰፊ እድሎችን ለመፍጠርና በመላው ምሥራቅ አፍሪካ ለላቀ ኢኮኖሚያዊና የኢንዱስትሪ ሉዓላዊነትን መሠረት ለመጣል ትልቅ ርምጃ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሁነት ነው ሲሉ ገልጸውታል።

የላሙ ወደብ-ደቡብ ሱዳን-ኢትዮጵያ-ኬንያ ኮሪደር አካል የሆነው ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያን እና ኬንያን በኢኮኖሚ ገመድ የሚያያይዝ ነው።

ፕሮጀክቱ ኢትዮጵያ ቀጣናውን በሰላም እና በልማት የማስተሳሰር ርዕይዋን በተግባር እያሳየች መሆኗን የሚያረጋግጥ ሲሆን ÷ ለሁለቱም ሀገራት የኃይል ዋስትና እና የኢንዱስትሪ ዕድገት ትልቅ መሠረት ይጥላል።

በዚሁ ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከጂቡቲው ፕሬዚዳንት ኢስማኤል ኦመር ጊሌ እና ባለሃብቱ አሊኮ ዳንጎቴ ጋር በመሆን፣ በጅቡቲ ዳመርጆግን ከኢትዮጵያ ደወሌ የሚያገናኘውን እና ታላቅ ስትራቴጂካዊ ኢንቨስትመንት የሆነውን አዲስ የተጣራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መስመር ዝርጋታ ይፋ አድርገዋል።

ይህ የቧንቧ መስመር ፕሮጀክት የኢትዮጵያን የነዳጅ አቅርቦት ቀልጣፋ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና ወጪ ቆጣቢ በማድረግ ረገድ የጎላ ድርሻ ይኖረዋል።

ኢትዮጵያ የሎጂስቲክስ ማዕከል የመሆን አቅሟን ከጎረቤት ሀገራት ጋር በጋራ እያረጋገጠች መሆኗን የሚያሳይም ነው ፕሮጀክቱ።

እንደ ኢትዮጵያ ያለ በፍጥነት እያደገ ያለ ትልቅ ሀገር ለኢኮኖሚው ግንባታ የነዳጅ እና የኃይል አቅርቦት ደህንነት ወሳኝ ነው።

ኢትዮጵያ እነዚህን ታላላቅ ፕሮጀክቶች ስትመራ እና ስትደግፍ የሚከተሉት ዋና ዋና ስትራቴጂዎች ጎልተው ይንጸባረቃሉ፡፡

ኢትዮጵያ የራሷን ዕድገት ከጎረቤት ሀገራት ዕድገት ጋር በማስተሳሰር የምሥራቅ አፍሪካን የጋራ ገበያ እና ሰላም በባለቤትነት እየመራች ትገኛለች።

አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካዊ አቅም እና በመሪዎች የጸና ቁርጠኝነት መፍታት እንደሚቻል እነዚህ ፕሮጀክቶች በብሩህ ሁኔታ ያሳያሉ።

ዛሬ በኬንያ የተከናወነው የላሙ የነዳጅ ማጣሪያ መሠረተ ድንጋይ ማስቀመጥ እና የዚህ ሳምንቱ የጂቡቲው የነዳጅ ቧንቧ መስመር ዝርጋታ ይፋ መሆን ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ መሪነት በግልጽ ያሳያሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንዲሁም የቀጣናው መሪዎች እያሳዩት ያለው ትብብርና መሰል ተነሳሽነት የኢትዮጵያን ታላቅነት እና የምሥራቅ አፍሪካን የብልጽግና አድማስ የሚያበስር ታሪካዊ ምዕራፍ ነው።

#ኢትዮጵያ #ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በሶስና አለማየሁ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.