የባህር በርን ማስመለስ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የቤት ስራ ነው – የአዲሰ አበባ ነዋሪዎች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 6፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የባህር በርን ማስመለስ የመንግሥት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ኢትዮጵያዊ የቤት ስራ ነው አሉ የአዲሰ አበባ ነዋሪዎች፡፡
ለፋና ዲጂታል አስተያየታቸውን የሰጡት የመዲናዋ ነዋሪዎች ኢትዮጵያ የጂኦግራፊ እስረኛ ሆና አትቀርም ብለዋል፡፡
የመዲናዋ ነዋሪ የሆኑት ግርማ ፍቃዱ ኢትዮጵያ በግፍ የተነጠቀችውን የባህር በር ማስመለስ ለመንግሰት ብቻ የሚተው ሳይሆን፤ የሁሉም ኢትዮጵያዊ የቤት ስራ መሆኑን ገልጸዋል።
ወ/ሮ አሳመነች ዘውዱ የተባሉት የመዲናዋ ነዋሪ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ያለአግባብ ባጣችው የባህር በር ምክንያት ለከፍተኛ የወደብ ኪራይ ተዳርጋለች ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያ ፍትሀዊ ባልሆነ መንገድ በተነጠቅችው የባህር በር ምክንያት በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ የምታወጣው የውጪ ምንዛሬ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የባህር በር ቢኖራት ለወደብ ኪራይ የምታወጣውን ከፍተኛ ወጪ ለተለያዩ ልማቶች በማዋል ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠር እንደሚቻል የገለጹት ደግሞ ስዩም ሀይለሚካኤል ናቸው፡፡
ቢረሳው ወርቄ የተባሉት የመዲናዋ ነዋሪ የባህር በር የማግኘት ጥያቄ የሁሉንም ህበረተስብ ክፍል ድጋፍ የሚጠይቅ ስራ ነው ብለዋል፡፡
በአብረሃም አበራ