መንግሥት አካታች የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር የወሰደው ርምጃ የሚደነቅ ነው – የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች
አዲስ አበባ፣ መስከረም 21፣ 2019 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠር የወሰደው ርምጃ የሚደነቅ ነው አሉ በአዲስ አበባ ከተማ በምክር ቤት አባልትነት የተካተቱ እና በሥራ አስፈጻሚነት የተመረጡ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች።
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የከተማ አስተዳደር መንግሥት ምስረታና 4ኛ ዙር የመክፈቻ ጉባዔውን በትናንትናው ዕለት አካሂዷል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እና የሕብረተሰብ ተሳትፎና የበጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኃላፊ ሆነው የተሰየሙት ወ/ሪት ጽዮን ደረጀ በዚህ ወቅት እንዳሉት÷ መንግሥት አካታችና አሳታፊ የፖለቲካ ምኅዳር ፈጥሯል።
የፖለቲካ ርዕዮተ-ዓለማዊ ልዩነት ሳይገድ በመሠረታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችና በልማት መስክ በትብብር ሥራት የአብን አቋም መሆኑን ገልጸዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የተፎካካሪ ፓርቲዎች ድምፅና ሀሳብ የሚካተትበት ዕድል መፈጠሩ ለመዲናዋ ልማትና ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዳለውም ለኢዜአ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ ሕዳሴ ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንትና የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባል ሱራፌል እሸቱ (ኢ/ር) በበኩላቸው÷ መንግሥት በጋራ ለመሥራት ያሳየውን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
ተቋማት ለዜጎች የሚሰጡትን አገልግሎት የበለጠ እንዲያጠናክሩ ጥረት እንደሚደረግና በሀገራዊ ጉዳዮች እንዲሁም በዜጎች ተጠቃሚነት ላይ ፓርቲያቸው በትብብር እንደሚሠራ አስታውቀዋል።
በቀጣይም በምክር ቤቱ በሚኖራቸው ቆይታ የታቀዱ ዕቅዶችና የተቀመጡ አቅጣጫዎች በኃላፊነት እንደሚወጡ ነው የገለጹት።