Fana: At a Speed of Life!

የሀገር መከላከያ ሠራዊት የጀግንነት ሕያው ምስክር

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 13፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የኢትዮጵያ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሀገር ሉዓላዊነትን የማስከበር፣ ዳር ድንበርን በአስደናቂ ጀግንነት የመጠበቅ እና ህዝባዊ ወገንተኝነትን የማረጋገጥ ረጅም እና አንጸባራቂ ታሪክ ያለው ተቋም ነው።
ሀገሪቱ በታሪክ አጋጣሚ የገጠሟትን አደጋዎች በጀግንነት ከመመከት ባሻገር ከሕዝብ ወገንተኝነቱና ከሀገራዊ ፍቅሩ የተነሳ የሀገር ዋስትና እና የፅናት ምልክት በመሆን ዘመናትን ተሻግሯል፡፡
ማንኛውንም የሀገርን ሰላምና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥሉ የውጭና የውስጥ ስጋቶችን በጀግንነት የመመከት አቅሙ ከፍተኛ ከመሆኑም በላይ በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ወቅት ከህዝቡ ጎን በመቆም የሚደርሱ ሰብዓዊ ጉዳቶችን የመቀነስና የህይወት አድን ስራዎችን በግንባር ቀደምትነት ያከናውናል።
ከሀገር ውስጥ ባሻገር በዓለም አቀፍና በአፍሪካ ህብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ በመሳተፍ የኢትዮጵያን የጀግንነትና የህዝባዊነት ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ አጉልቷል።
የመደመር መንግሥት ለመከላከያ ሠራዊቱ ግንባታና ዘመናዊነት አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ሲሆን÷ በዚህም ትንኮሳን በሩቅ ከማስቀረት ባለፈ ውጊያን በትንሽ ኪሳራ በድል ማጠናቀቅ የሚችል ሰራዊት ተገንብቷል፡፡
ሠራዊቱን በዘመናዊ የጦር መሳሪያዎች፣ በዲጂታል ቴክኖሎጂዎችና በሰው ኃይል ስልጠና በማደራጀት ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪ የጦር ኃይል እንዲሆን ተደርጓል።
የአየር ኃይል፣ የባህር ኃይል እና የሳይበር ደህንነት ክፍሎች በአዲስ መልክ እንዲደራጁና እንዲጠናከሩ በማድረግ ዘመኑን የዋጀ ሰራዊት እንዲሆን ተደርጓል፡፡
በመከላከያ ሠራዊቱ ስር የሚገኙ ኢንዱስትሪዎችን በመልሶ ማደራጀት፣ ሠራዊቱ ለሀገር ልማት ቀጥተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክትበት ሁኔታ ተፈጥሯል።
በዚህም በግብርና፣ በኮንስትራክሽን እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች ሠራዊቱ ያከናወናቸው ተግባራት የሚደነቁ ናቸው።
የሠራዊቱን አባላት ሕይወትና የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ ለማሻሻል የሚያስችሉ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ የጤና እና የትምህርት አቅርቦት ማሻሻያ ስራዎች ተከናውነዋል።
ሠራዊቱ ከፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ሆኖ የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም ብቻ የሚያስጠብቅ፣ ሙያዊ ብቃትና ሥነ ምግባርን የተላበሰ እንዲሁም ብሔራዊ ስብጥርን በጠበቀ ሁኔታ የተደራጀ የህዝብ ተቋም እንዲሆን ውጤታማ የሆኑ ሰፊ የማሻሻያ ስራዎች ተሰርተዋል።
የኢትዮጵያ ሀገር መከላከያ ሠራዊት የረጅም ዘመን የጀግንነትና የሕዝባዊነት ታሪክ ውጤት ነው።
ከመደመር እሳቤ ጋር ተጣጥሞ በተሰራው ተቋማዊ ማሻሻያ ደግሞ ሠራዊቱ ሉዓላዊነትን የማስከበር አቅሙን ከማሳደጉም በላይ ለሀገራዊ ብልጽግና የጸና መሰረት መሆኑን አስመስክሯል።
በመልካም ፈቃዱ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.