”አየር አፈሯ ይባረክ ፤ ምንጊዜም ስሟ ይታደስ …”
አዲስ አበባ፣ መስከረም 24፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ታላቅ ሃገር ህልውና፣ ክብር እና ብሔራዊ ጥቅም የሚወሰነው የዳር ድንበሯን ደህንነት ሌሊትና ቀን ሳይተኛ በሚጠብቅ፣ ታሪክ ሰሪና ታሪክ አዳሽ በሆነ ኃያል ሠራዊት ነው።
ህዳር 16 ቀን 1993 ዓ.ም የሀገር ፍቅር ስሜት ጫፍ በረገጠበት እና የአንድነት መንፈስ በተቀጣጠለበት ወቅት የተወለደው “የኩሩ ሕዝቦች መኖሪያ” የተሰኘው የመከላከያ ሠራዊት መሪ መዝሙር ፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት በደም እና በአጥንት የማስከበር ፅኑ ተምሳሌት ነው።
ይህ መዝሙር ተራ የስነ-ጽሑፍ ስራ ሳይሆን፤ የሠራዊታችንን የአሸናፊነት ስነ-ልቦና፣ የጀግንነት ጀብዱ እና የጠላትን አከርካሪ የመስበር የማይናወጥ ቁርጠኝነት የሚያሳይ የውጊያ አዋጅ ነው።
በዚሁ ታሪካዊ መዝሙር ስንኞች እና በሠራዊቱ የዕለት ተዕለት የጦር ሜዳ ጀብዱ ላይ በመመስረት ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም እና አሸናፊነት የምናይበት ጥልቅ አዕማድ በስንኞቹ ውስጥ ጸንቶ ቆሟል።
“በደም አሻራሽ አትመው፤ ሕዝቦች ለሰጡን አደራ፣ለሕገ-መንግሥታችን ክብር፤ ታጥቀን ቆመናል በጋራ።”
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሀገርን ዳር ድንበር የሚጠብቀው በወረቀት ላይ በሰፈረ ውል እና ፊርማ ብቻ ሳይሆን፣ በደም አሻራ እና በአጥንት በተከፈለ ክቡር መስዋዕትነት ነው።
ከሕዝብ የወጣ የሕዝብ ልጅ በመሆኑ፣ የተሰጠውን የሀገር አደራ ለመጠበቅ አንዳችም ወደኋላ አይልም።
በሀገሪቱ ዙሪያ የጥፋት እሳት ቢነድና ፈተናዎች ቢበረቱም፣ ሠራዊቱ ያንን የፈተና እሳት ጥሶ የማለፍ እና የማይሞት ታሪክ የመስራት ልዕለ-ሰብአዊ ብቃት አለው።
ከምድር እስከ አየር የጠላትን እንቅስቃሴ የሚቆጣጠረው ይህ ፅኑ አቋም፣ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም በማስከበር ረገድ ቀዳሚውን ሚና ይጫወታል።
“የማንጨበጥ ነበልባል፤ እሳት ነን ለጠላታችን ፣ ፍሙ ከርቀት ይፋጃል፤ ብረት ያቀልጣል ክንዳችን።”
የኢትዮጵያ ታሪክ በግልጽ እንደሚመሰክረው፣ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ለመናድ እና ሉዓላዊነቷን ለማደፍረስ ከሩቅ የሚመጡ ባዳዎች እና ከውስጥ የሚበቅሉ ባንዳዎች ሁልጊዜም አይጠፉም።
ሆኖም ግን፣ መከላከያ ሠራዊቱ ለእነዚህ እኩይ ኃይሎች “የማይጨበጥ ነበልባል” እና “ብረት የሚያቀልጥ ክንድ” ሆኖባቸዋል።
የሉዓላዊነትን ቀይ መስመር ለማለፍ የሞከሩ የውጭ ወራሪዎችንም ሆነ፣ የሀገርን የጀርባ አጥንት ለመስበር የተንቀሳቀሱ የውስጥ ባንዳዎችን አከርካሪ በመስበር የኢትዮጵያን ዘላለማዊ አሸናፊነት አስመስክሯል።
የሠራዊቱ የጀግንነት ወኔ ጠላትን ከሩቅ የሚያርበደብድ ፍም በመሆኑ፣ ባንዳው ጨርቄን ማቄን ሳይል በሩጫ ላይ እንዲሆን አድርጓል።
“የአበው የአርበኝነት ቅርስ፤ የነፃነት ገድል ፋና ፣ ወደ ትውልድ ተሸጋግሮ፤ ወርሶት ፀንቷል እንደገና።”
የአባቶቻችን የአርበኝነት ቅርስ እና የነፃነት ገድል ፋና ዛሬም በሠራዊቱ ልብ ውስጥ ህያው ሆኖ ይነዳል።
ሠራዊቱ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ በማውለብለብ፣ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በቀጣናውም ጭምር አስከብሯል።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ያላትን የጂኦ-ፖለቲካዊ የበላይነት እና ብሔራዊ ጥቅም ለማስጠበቅ፣ የሠራዊቱ አስተማማኝነት የማይተካ ምሰሶ ነው።
ሰንደቋ በኩራት እንዲውለበለብና ጠላቶቿ በፍርሃት እንዲመለከቷት ያደረገው ይሄው የማይበገረው ክንድ ነው።
“ኢትዮጵያ በኛ ደም ደምቃ፤ በአፅማችን ፍላፅ ተማግራ ፣ እንደታፈረች እንድትኖር፤ ከዘመን ዘመን ተከብራ። ከመሞት በላይ እንሙት፤ ደማችን ሺ ግዜ ይፍሰስ…”
የዚህ ሁሉ የፅናት ተጋድሎ ማሳረጊያ፣ ይህ የመጨረሻው የመዝሙሩ ስንኝ የሚያሳየው እጅግ የላቀ የስነ-ልቦና ጥንካሬ ነው።
“ከመሞት በላይ መሞት” ማለት ስለ ሀገር ክብር ሲባል ራስን ሙሉ በሙሉ አሳልፎ መስጠት፣ ለአፈር እና ለአየር መቀደስ ሲባል አጥንትን ከስክሶ ደምን ማፍሰስ ማለት ነው።
ትልቅ ሕዝብ፣ ትልቅ ሀገር እና ታላቅ ርዕይ ያላት ኢትዮጵያ ዛሬም ታፍራ እና ተከብራ ከዘመን ዘመን እንድትሻገር፣ የጀግናው ሠራዊት አፅም እንደ ምሰሶ ሆኖ ሀገሪቱን ደግፏታል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ፍፁም የማይደፈርና የማይደራደርበት መሆኑ የሚረጋገጠው፣ ሠራዊቱ ለሀገሩ ባለው በዚህ ጥልቅ የመስዋዕትነት ትርጉም ነው።
በፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ባልደረባ ተፈራ መኮንን የተፃፈው “የኩሩ ሕዝቦች መኖሪያ” መሪ መዝሙር ህያው ምስክርነት፣ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የአንድነት፣ የጥንካሬ እና የዘላለማዊ አሸናፊነት መገለጫ ነው።
ባዳን እና ባንዳን እያርበደበደ፣ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም ሳያስደፍር፣ ሰንደቅ ዓላማዋን ከፍ አድርጎ ሉዓላዊነቷን ያስከበረው ይሄው የሕዝብ አለኝታ የሆነው ሠራዊታችን ነው።
በደማቸው አድምቀው፣ በአጥንታቸው ማግረው የኢትዮጵያን ስም ለዘላለም የሚያድሱት የሀገራችን መከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የኢትዮጵያ ህልውና ታማኝ ጠባቂዎች እና የደማቅ ታሪካችን ወርቃማ ገጾች ናቸው!
በኃይለኢየሱስ መኮንን