Fana: At a Speed of Life!

በኦሮሚያ ክልል ለአዲሱ ዓመት በዓል የፍጆታ ዕቃዎችን በበቂ ሁኔታ ለማቅረብ ዝግጅት ተደርጓል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል ለመጪው 2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት በዓል መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች አቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጓል አለ የክልሉ ንግድ ቢሮ፡፡

የቢሮው ም/ኃላፊ ተስፋዬ ገሹ በሰጡት መግለጫ÷ በበዓሉ ወቅት የሚከሰት የምርት እጥረት እንዳይኖር በዞኖችና በከተሞች ደረጃ በቂ ምርቶች እንዲቀርቡ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የምርት አቅርቦቱን ይበልጥ ለማሳለጥ በ914 የቅዳሜና እሑድ ገበያዎች መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎች በኤግዚቢሽን መልክ ለሸማቾች እየቀረቡ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሰረትም ከ420 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል፣ 359 ሺህ ቶን አትክልትና ፍራፍሬ፣ 2 ነጥብ 2 ሚሊየን ሊትር የምግብ ዘይት እንዲሁም ከ24 ሺህ ኩንታል በላይ ስኳር ለገበያ መቅረቡን ነው ያብራሩት፡፡

በሌላ በኩል ለበዓሉ በቂ የእርድ እንስሳት ለገበያ እንዲቀርብ አስፈላጊው የገበያ ትስስር መፈጠሩን ምክትል ሃላፊው አመልክተዋል፡፡

በሕገ ወጥ ነጋዴዎችና ደላላዎች ምክንያት የአቅርቦት እጥረት እንዳይፈጠር በሁሉም ዘርፍ ላይ ጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

ሕብረተሰቡ ለበዓሉ በቂ ምርት መኖሩን ተገንዝቦ በተረጋጋ ሁኔታ እንዲሸምት ያስገነዘቡት ም/ሃላፊው÷ ነጋዴዎች አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ከማድረግ እንዲቆጠቡ አሳስበዋል፡፡

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.