Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት በመሰራቱ የተማሪዎች ውጤት ተሻሽሏል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በአዲስ አበባ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት በመሰራቱ የተማሪዎች ውጤት እየተሻሻለ መጥቷል አሉ የአስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ።

ከንቲባዋ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው÷ ዛሬ 33ኛውን ከተማ አቀፍ የትምህርት ጉባዔ “ብሩህ ነገን በዛሬ አዕምሮዎች” በሚል መሪ ሃሳብ አስጀምረናል ብለዋል።

ጉባዔው በየዓመቱ የሚካሄደው የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ፣ ተደራሽነትን ለማስፋት፣ የመማር ማስተማር ሒደቱን ጤናማ እና ውጤታማ ለማድረግ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በዘርፉ የተሰሩትን ጠንካራ ሥራዎች ልምድ የምንቀምርበት፣ የሚታረሙትንም ለይቶ በጋራ መፍትሄ የምንሰጥበትና በጋራ እቅጣጫ የምንይዝበት ጉባዔ ነው ሲሉም አመልክተዋል።

አሁን ላይ በመዲናዋ የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ውጤት ወደ 33 በመቶ መሻሻል ማሳየቱን ጠቅሰው÷ ነገር ግን በቀጣይ ከፍ ያለ ውጤት እንጠብቃለን፤ ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

መምህራንና ባለድረሻ አካላት በእልህ ሰርተን መፍጠር የሚችሉ፣ ችግር የሚፈቱ፣ በሥነ ምግባር የታነፁና እውቀት የታጠቁ ተማሪዎችን በብዛት ለመፍጠር መረባረብ አለብን ነው ያሉት፡፡

በከተማ አስተዳደሩ ዋናው ኢንቨስትመንት ትምህርት መሆኑን በመገንዘብ ከፍተኛው በጀት ለትምህርት ዘርፍ እንዲውል መደረጉን አብራርተዋል፡፡

ትውልድ ላይ ከስር መሰረቱ መስራት ወሳኝ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች ፥ የእዕምሮ እድገት በጨቅላ ሕፃንነት ወቅት የሚከሰት በመሆኑ ቀዳማይ ልጅነት ላይ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ አግባብ ከመሰረቱ ጀምረን እየሰራን በአንደኛ ደረጃ እንዲሁም በሁለተኛ ደረጃ ት/ ቤቶች ላይ ከፍተኛ ውጤት እና በዲሲፕሊን የታነፀ ትውልድ እንጠብቃለን ነው ያሉት።

እስካሁን ለተገኘው ውጤት ሁሉምን ባለድርሻ አካላት አመስግነው ÷ በቀጣይ በእውቀት የበለፀጉ፣ በሥነ ምግባር የታነፁና አልቀው የሚሰሩ ተማሪዎች ለመፍጠር ከልብ ዋጋ ከፍሎ በትብብር መስራት ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.