Fana: At a Speed of Life!

ከልመናና ጥገኝነት በተላቀቀው ታሪካዊ መንገዳችን እውነተኛ ሉዓላዊነትን እያረጋገጥን ነው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)

አዲስ አበባ፣ጳጉሜን 1፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከልመናና ጥገኝነት በተላቀቀው አዲስ እና ታሪካዊ መንገዳችን እውነተኛ ሉዓላዊነትን እያረጋገጥን ነው አሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዛሬው ዕለት እየተከበረ የሚገኘውን የእመርታ ቀን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የእመርታ ጉዟችን ለመጪው ዓመት የሰነቀው ተስፋ እጅግ ግዙፍ ነው ብለዋል፡፡

በሚሊየን በሚቆጠር ዶላር ስንዴ ከማስገባት ተነስተን፤ ዛሬ የአፍሪካ ቀዳሚ ስንዴ አምራች በመሆን የሚሊየን ዶላሮችን ወጪ ማስቀረት ችለናል ነው ያሉት።

አባቶቻችን የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በደምና በአጥንታቸው አስከብረው ታላቅ ሀገር ማውረሳቸውን በማውሳት፤ ዛሬ ደግሞ እውነተኛ ሉዓላዊነትን እያረጋገጥን ያለነው ከልመናና ከጥገኝነት በተላቀቀው አዲሱና ታሪካዊው መንገዳችን ነው ብለዋል፡፡

በሌማት ትሩፋት የምግብ ዋስትናን በተግባር እያረጋገጥን፤ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ አዳዲስ ኢንዱስትሪዎችን በማስፋፋትና የሥራ ዕድል በመፍጠር ሉዓላዊነታችንን እያረጋገጥን እንገኛለን ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም የማይደፈሩና አይነኬ ይባልላቸው የነበሩ ከባድ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ውሳኔዎችን በቁርጠኝነት በመተግበር የሀገራችንን ኢኮኖሚ በፅኑ መሠረት ላይ እየገነባን እንገኛለን ብለዋል።

እነዚህ ሁሉ ታላላቅ ድሎች ኢትዮጵያ በሚያጋጥሟት ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ሸብረክ ሳትል በፅናት መጓዝ መቻሏን የሚያረጋግጡ ህያው ምስክሮች ናቸው ሲሉ አውስተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው፤ ይህ የእመርታ ጉዟችን ለመጪው ዓመት የሰነቀው ተስፋ እጅግ ግዙፍ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.