የቀጣናው ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለኢትዮጵያ የባሕር በር በማመቻቸት ህልውናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው – ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) የቀጣናው ሀገራት በሰላማዊ እና ሀብትን በጋራ በመጠቀም መርህ ለኢትዮጵያ የባሕር በር በማመቻቸት የጋራ ህልውናቸውን ማረጋገጥ አለባቸው አሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)።
ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ከቀይ ባሕር ጋር የማይነጣጠል ታሪካዊ ቁርኝት ያላትና የባሕር በር ጥያቄዋም የ130 ሚሊየን ሕዝብ የህልውና አጀንዳ ነው፡፡
ከጥንት ጀምሮ ቀይ ባሕር የኢትዮጵያ ግዛት ወሰን አካል ሆኖ መኖሩን ገልጸው ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎችም የራሳቸውን መገበያያ ገንዘብ በመጠቀም በቀይ ባሕር በኩል እስከ ሕንድ ውቅያኖስ ድረስ ይነግዱ እንደነበር እና ከ1950ዎቹ በኋላም አሰብና ምፅዋ የኢትዮጵያ ዋና የባሕር በር ወደቦች ሆነው ማገልገላቸውን አስታውሰዋል።
ሆኖም ህጋዊ መሰረት በሌለው ሁኔታ እንዲሁም ያለ ሕዝብ ይሁንታ እና ያለ በቂ ጥናት ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድታጣ መደረጉንም አብራርተዋል።
በባሕር ንግድ በተሳሰረች ዓለም ውስጥ 130 ሚሊየን ሕዝብን ይዞ ያለ ምንም የባሕር መውጫ ረጅም ጉዞ ማሰብ አይቻልም ብለዋል፡፡
የባሕር በር ጉዳይ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ በቁጭት የቆየ መሆኑን ጠቅሰው፥ አሁን ያለው መንግሥት ኃላፊነት የሚሰማው በመሆኑ የባሕር በር አጀንዳን ፊት ለፊት ይዞ መጥቷል ነው ያሉት፡፡
የባሕር በር ለንግድ ብቻ ሳይሆን ሀገርን ከጥቃት ለመከላከልም ወሳኝ የብሔራዊ ደህንነት ዓምድ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
የባሕር በር ጥያቄ በሰላማዊ መንገድና የጋራ ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት ጠቅሰው፣ ጉዳዩ ትውልድ የማይተወው የህልውና አጀንዳ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
በቀይ ባሕር ዙሪያ ያሉ ሀገራት የሕዝብ ብዛትና ኢኮኖሚ ተደምሮ የኢትዮጵያን ግማሽ አቅም እንኳ እንደማይደርስ ጠቁመው፤ የኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር መምጣት ለእነዚህ ሀገራትም ትሩፋት እንደሚሆን ገልጸዋል።
ቀጣናው የኃያላን ሀገራት መራኮቻና የተለዋዋጭ ሁኔታዎች ሰለባ መሆኑን ጠቅሰው፥ ከዚህ አኳያ የቀጣናው ሀገራት በጋራ መልማት የምርጫ ጉዳይ አለመሆኑን ተናግረዋል።
የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት በመቀነስ በኢኮኖሚና በታሪክ የተሳሰረውን ሕዝባቸውን ጥቅምና ደህንነት ለማስጠበቅ ከኢትዮጵያ ጋር መስራት እንደሚገባቸውም ነው የተናገሩት።
ኢትዮጵያ በአካባቢው ግዙፍ ኢኮኖሚ የምታንቀሳቅስ መሆኗ ፋይዳው ድንበር ዘለል መሆኑን አንስተው፤ ከባሕር በር ተነጥላ ልትኖር ስለማትችል የአካባቢው ሀገራት የመውጫ በር ሊሰጧት ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የቀጣናው ሀገራት በሰላማዊ መንገድ የውጭ ኃይሎችን ጣልቃ ገብነት በመከላከልና ሀብትን በጋራ በመጠቀም መርህ ለኢትዮጵያ የባሕር በር በማመቻቸት የጋራ ህልውናቸውን ማረጋገጥ እንዳለባቸው ጠቁመዋል።