በኦሮሚያ ክልል ለአዲሱ ዓመት እስካሁን ከ400 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ማዕድ ተጋርቷል
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) በኦሮሚያ ክልል የ2019 ዓ.ም ዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ እስካሁን ከ400 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ማዕድ ተጋርቷል አለ የክልሉ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳዮች ቢሮ።
በቢሮው የማኅበራዊ ጥበቃ ዳይሬክተር አብዱላሂ አሕመድ ለፋና ዲጂታል እንዳሉት÷ የዘመን መለወጫ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከጳጉሜን 1 ቀን 2018 ዓ.ም እስከ መስከረም 1 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ ለ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ዜጎች ማዕድ ለማጋራት ታቅዷል።
በዚህም መሠረት ከጳጉሜን 1 ጀምሮ እስከ ጳጉሜን 3 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ ከ400 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የበዓል መዋያ ድጋፍ መደረጉን ነው የገለጹት።
በዛሬው ዕለትም የኅብር ቀንን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ አካባቢዎች ማዕድ የማጋራት ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በክልሉ በዚህ ዓመት ለ7 ሚሊየን ዜጎች ድጋፍ ለመስጠት መታቀዱን ጠቁመው÷ ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከ2 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች 36 ቢሊየን ብር የሚያወጣ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።
ድጋፉ አዳዲስ ቤቶችን መገንባትና ማደስ፣ የምግብ አቅርቦት፣ አልባሳት፣ የትምህርት ቁሳቁስ፣ የገንዘብ ድጋፍና ለአካል ጉዳተኞች የሚያገለግሉ መሣሪያዎችን ያካተተ ነው ብለዋል፡፡
በሲፈን መገርሳ