የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ እንድንሆን አስችሎናል – የቆርኬ ዲቢሳ ነዋሪዎች
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከተጠናቀቀ በኋላ ለዘመናት ስንናፍቀው የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት ችለናል አሉ በሸገር ከተማ ፉሪ ክፍለ ከተማ የቆርኬ ዲቢሳ አካባቢ ነዋሪዎች፡፡
ነዋሪዎች ላለፉት 19 ዓመታት የኤሌክትሪክ ሃይል መሠረተ ልማት ለማግኘት ሲጠይቁ መቆየታቸውን ለፋና ዲጂታል ተናግረዋል፡፡
ይህ ለዘመናት የቆየ የኤሌክትሪክ ኃይል የማግኘት ፍላጎትም ኢትዮጵያውያን በትብብር ለስኬት ባበቁት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ እውን ሆኗል ብለዋል፡፡
ወይዘሮ ወይቱ አበበ የተባሉት ነዋሪ ከዚህ በፊት በተለይ በክረምት ወቅት የማገዶ እንጨትን ተጠቅሞ ማብሰል እጅግ አድካሚ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡
አሁን ላይ ግን ሥራን ለመሥራት ግዴታ ቀንን ብቻ መጠበቅ እንደማያስፈልግና በኤሌክትሪክ ኃይል ቀንም ማታም መሥራት መቻላቸውን ተናግረዋል፡፡
ከሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በኋላ የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ በመሆናቸው የአኗኗር ዘይቤያቸው እንደተሻሻለና በዚህም እጅግ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ ኩምሳ በቀለ በበኩላቸው ÷ ከዚህ ቀደም ይኖሩበት ከነበረው አካባቢ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት በሚል አሁን ያሉበት ሰፈር መምጣታቸውን ያስታውሳሉ፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቁን ተከትሎ ለዘመናት ሲመኙት የነበረውን የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት በመቻላቸው መደሰታቸውን ያብራራሉ፡፡
አካባቢው ላይ ኤሌክትሪክ ከመግባቱ በፊት በሻማ እና ኩራዝ ለማጥናት ስትሞክር ይከብዳት እንደነበር የተናገረችው ደግሞ ሕፃን ሜቲ ኩምሳ ናት፡፡
አሁን ላይ ግን ትምህርቷን ማጥናት ብቻ ሳይሆን በቴሌቪዥን የሚተላለፉ ትምህርታዊ መሰናዶዎችን መከታተል እንደቻለች ተናግራለች፡፡
ነዋሪዎቹ ኢትዮጵያውያን ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ ያሳዩትን ሕብረት፣ ጽናትና አንድነት በሌሎች ፕሮጀክቶችና ሀገራዊ ዕቅዶች ላይ መተግበር እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡
በእመቤት ሲሳይ