Fana: At a Speed of Life!

በኅብረ ቀለማት የተዋበው ኢትዮጵያዊነት

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2018 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያውያን ብዝሃ ማንነት ባላቸው ብሔሮች ብሔረሰቦች የተገነባች ሀገር ናት፤ ይህም የውበትና ጥንካሬ ምንጭ ሆኗል፡፡
ኅብር ልዩነትን ባለመካድ የተለያዩ የሃይማኖት፣ የባሕል፣ የቋንቋ እንዲሁም የአስተሳሰብ ቀለሞች በአንድ ሲቀመጡ እንደሚኖራቸው የተዋበ ውህደት ነው፡፡
ብዝሃ ማንነት በርካታ ባሕሎችን፣ ችግር መፍቻ ጥበቦችን እንድንማማርባቸውና እንድንዋዋሳቸው ዕድል ይከፍትልናል፡፡
በየአካባቢው እንደ የማህበረሰቡ ባህል መሠረት በጋራ የመሰብሰብ፣ በሀዘንና በደስታ አብሮ በመቆም ችግሮቹን የሚፈታባቸው መንገዶች አሉት፡፡ ይህም ተመሳሳይነት ላይ የተመረኮዘ ሳይሆን አብሮ መኖርን፣ መረዳዳትና መከባበርን መሰረት በማድረግ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን በየንግግሮቻቸው መካከል ጣል የሚያደርጓቸው ምሳሌያዊ አነጋገሮችም የኅብርን በጎ መልክ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ድር ቢያብር አንበሳ ያስር የሚሉት ኢትዮጵያውያን ልዩ የሆኑ መገለጫዎችን ተቀብሎ፣ ተከባብሮና አስማምቶ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ አጋምዶ በጋራ የመቆም ተምሳሌቶች ናቸው፡፡
በዓድዋ ጦርነት ወቅት የሀሳብ ልዩነት የነበራቸው፣ የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ ገብተው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሀገር ወራሪ ጠላት ሲመጣ እምቢ ለሀገሬ ብለው የውስጥ ጉዳያቸውን በይደር አቆይተው፣ ለሀገራቸው በጋራ ዘምተዋል፡፡
የየራሳቸውን ጥበብ ይዘው በጀግንነት ተዋግተው በዓድዋ ተራሮች ጠላትን ድል ነስተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን ይህንን ኅብር በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብም ደግመውታል፤ በተለያየ ባሕል፣ አመለካከት እንዲሁም የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ለሀገር ብሔራዊ ጥቅም በጋራ ቆመው፣ የውጪ ጫናን ተቋቁመው፣ የአትችሉምን ድምጽ አሸንፈው በራስ አቅም ለውጤት አብቅተውታል፡፡
የኢትዮጵያውያን የህብረት ውጤት የሆነው ዳግማዊ ዓድዋን የሚወክለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከተመረቀ ዛሬ አንደኛ ዓመቱን ይዟል፡፡
ይህም የኢትዮጵያን በጋራ የመቆምና ጀምሮ የመጨረስ አቅም ለዓለም ያረጋገጠ፣ ለትውልድ የሚተርፍ በጎ አሻራን ያስቀመጠ ታሪካዊ ክስተት ሆኗል፡፡
በመሆኑም አበቦች ድምቀታቸው በኅብረ ቀለማት መዋባቸው ደግሞም ሰብሰብ ብለው መታየታቸው እንደመሆኑ ባለ ብዝሃ ማንነት የሆኑት ኢትዮጵያውያንም በጋራ መቆማቸው ሕብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያን በማይናጋ ጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም ሚናው ትልቅ ነው፡፡
በቤተልሔም ግርማ
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.