ኢትዮጵያና ሕንድ ጥልቅ ታሪካዊ ትስስርና የዘመናት የባህል ግንኙነት አላቸው – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)
አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያና ሕንድ ጥልቅ ታሪካዊ ትስስርና የዘመናት የባህል ግንኙነት አላቸው አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) ከብሪክስ የመሪዎች ጉባዔ ጎን ለጎን ከህንድ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ ጋር የኢትዮጵያ ሕንድ አጋርነትን ይበልጥ ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
የመከላከያ ትብብርን ማሳደግ፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር፣ የአቅም ግንባታ፣ የማዕድን ልማት እና ወደ ኮፕ 32 በሚደረገው ጉዞ ላይ ያለንን አጋርነት ማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነበር ውይይት ማድረጋቸውን በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል።
እነዚህ መስኮች በተግባር የታገዘ ትብብራችንን ይበልጥ ለማሳደግ እና ለሕዝቦቻችን አዳዲስ ዕድሎችን ለመፍጠር ከፍተኛ አቅም አላቸው ነው ያሉት።
ኢትዮጵያና ሕንድ ጥልቅ ታሪካዊ ትስስር፣ የዘመናት የባህል ግንኙነት እና በሕዝቦቻችን መካከል ጠንካራ ወዳጅነት አለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር)፤ ይሁን እንጂ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያሉት በርካታ አቅሞች ገና ያልተነኩ ናቸው ብለዋል።
ያለንን የጋራ ታሪክና ትብብር በቴክኖሎጂ፣ በክህሎት፣ በኢንቨስትመንት፣ በዘላቂ ልማት እና ይበልጥ በጠነከረ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይ ወደተመሠረተና የላቀ የጋራ ተጠቃሚነትን ወደሚያረጋግጥ አጋርነት ለመለወጥ አሁን ትክክለኛው ጊዜ ነው ሲሉም አብራርተዋል፡፡