ለቃል ታምኖ በተግባር መጽናት፤ የመደመር መንግሥት መገለጫ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) በኢትዮጵያውያን ዘንድ ለቃል ትልቅ ቦታ ይሰጣል፤ ስነ ቃሎች ሳይቀር ለቃል የምሰጠውን ቦታ የሚሳዩ ናቸው፡፡ የተናገሩት ከሚጠፋ የወለዱት ይጥፋ ይባላል፤ ለቃል ምን ያህል ቦታ እንደምንሰጥ ከዚህ የላቀ ማሳያ አይኖርም፡፡
የትናንት ተግባር ለዛሬ ምስክርነት የሚቆም በመሆኑ የለውጡ መንግሥት ባለፉት ዓመታት ያስመዘገባቸው ስኬቶች ሌሎች በአስርት ዓመታት እንኳ ሊከውኗቸው የማይችሉ ታላላቅ ስኬቶች ናቸው፡፡
የግብርና ዘርፉን በዘመናዊ ሜካናይዝድ መሳሪያዎች የታገዘ በማድረግ፣ ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት አምርታ በምግብ ራሷን ከመቻል ባሻገር ወደ ሌሎች ሀገራት ምርትን በመላክ የውጪ ምንዛሬን የምታሳድግበትን አቅም ፈጥሯል፡፡
ዜጎችን በማዘመንና ክህሎትን በማጎልበት ለትውልድ የሚትተርፍ ሀገርን በማኖር የሚያምነው የመደመር መንግሥት የዲጂታል 2025ን በውጤት አጠናቅቆ የዲጂታል 2030 ስትራቴጂን በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡
ከተሞችን በኮሪደር ልማቶች በማስዋብ፣ ቅርሶችንም ባሉበት የእድሳት ስራዎች በመስራት እንዲሁም እንደ ገበታ ለትውልድ፣ ገበታ ለሸገርና ገበታ ለሀገር ያሉ የቱሪዝም ገጽታን በዘላቂነት የቀየሩ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡
ይህን ተከትሎ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች በኢትዮጵያ እንዲካሄዱ ሆኗል፡፡ የውጪ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች እንዲሁም ጎብኚዎች ኢትዮጵያ እየተገኙ፣ ያልቻሉትም ያላቸውን ጥልቅ ፍላጎት እንዲገልጹ አድርጓል፡፡
ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ከነበረበት ላይ አንስቶ በተገቢው መንገድ እንዲጠናቀቅ በተደረገ ማግስት የጉባ ላይ ብስራቶች ለኢትዮጵውያን አብስሯል፡፡
ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ለዓመታት የተነጠቀችውን የባህር በር ባለቤትነቷን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ፣ የጋራ ተጠቃሚነትን ባማከለ፣ ዓለም አቀፍ ህግን ባከበረ መልኩ ለማሳካት የሚሰራው ስራ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ከማስጠበቅ ባሻገር በፍትሀዊነት ላይ ያለውን አመኔታ ያሳየ ነው፡፡
ኢትዮጵያ በሚኖራት የውጪ ግንኙነት የብሔራዊ ጥቅሟን የሚስጠብቁ በጋራ ማደግን መነሻ ያደረጉ እንደ ብሪክስ ያሉ ስምምነቶች በለውጡ መንግሥት የተደረጉ ናቸው፡፡
በመሆኑም በዚህ ሂደት ለኢትዮጵያ ዘላቂ እድገትን እንደሚያመጡ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪነቷን እንደሚያስጠብቁ ከሚታመንባቸው ጋር ኢትዮጵያ በጋራ እንደምትሰራ ያመለከቱ ናቸው፡፡
መንግሥታት ወደ ስልጣን ሲመጡ ህዝብ በመኖር ውስጥ አካሄዶቻቸውን ይገመግማል፤ የምርጫውን ልክነትና ስህተትነት ይመዝናል፤ በቃሉ ለታመነለትም ዳግም ድምጹን ይሰጣል፡፡
በመሆኑም የተደረጉትን በጎ ለውጦች የተገነዘበ፣ ቃል በተግባር ሲገለጥ የተመለከተ ህዝብ በ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ በነቂስ ወጥቶ ድምጽ በመስጠት የመሰከረውም ይህንኑ መሬት ላይ ያለ ሀቅ ነው፡፡
በቤተልሔም ግርማ