Fana: At a Speed of Life!

የወል ትርክት ለብሔራዊ መግባባት

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) የአንድ ሀገር ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት የሚመሠረተው በዜጎቿ በሚገነባ የጋራ ታሪክና ስምምነት ላይ ነው።

የሕዝቦች የወል ትርክት ልዩነቶችን አክብሮ፣ ሁሉንም ዜጋ እኩል የሚያስተናግድ የእኛነት ስሜት የሚፈጥርና ልዩነቶች ወደ ግጭት እንዳያመሩ የሚያደርግ ነው፡፡

የረጅም ዘመን ታሪክና የብዝሃ ባህል ባለቤት እንዲሁም የነፃነት ተምሳሌት የሆነችው ሀገራችን ኢትዮጵያ ሕዝቧን አስተባብራ በተፈጥሮ ሀብቷ ዘላቂ ብልጽግናን እንድታረጋግጥ የወል ትርክትን ማንበር ወሳኝ ነው፡፡

ቀደም ባሉት ዓመታት ልዩነቶችን እንደ ውበት ከመቁጠር ይልቅ ጽንፍ በመያዝ ለግጭት የሚጋብዙ እሳቤዎች ኢትዮጵያ ባላት የማደግ አቅም ልክ እንዳታድግ ሲያሰናክሉ ቆይተዋል፡፡

የመደመር መንግሥት እነዚህን ልዩነቶች አክብሮ፤ ሁለንተናዊ ብልጽግናን እውን ለማድረግ የሚያስችል ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን ለማጽናት እየሰራ ይገኛል፡፡

ይህ የወል ትርክት የማስረጽ ጉዞ የሁሉንም ማህበረሰብ ባህል፣ የጋራ እሴትና ታሪክ እንዲሁም የወደፊት ራዕይ በማስተሳሰር ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።

በዚህ ረገድ በዘመናት መካከል በሕዝቡ ዘንድ የተፈጠሩ ቁርሾዎችን በማድመጥ የጋራ መፍትሄ ለማሰጠት የተካሄደው ሀገራዊ ምክክር ለዚህ የወል ትርክት ግንባታ ከፍተኛ አበርክቶ ያለው ነው፡፡

ይህም ቁርሾዎች የግጭት መንስኤ እንዳይሆኑ በዘላቂነት በመፍታት፤ ሕዝቡ በሀገራዊ ጉዳይ ለአንድ ዓላማ እንዲሰለፍና የሁሉም ታሪክ፣ ባህልና አስተዋፅኦ እኩል እውቅና እንዲያገኝ የሚያስችል ነው፡፡

የወል ትርክት ያለፈ ታሪክ ብቻ ሳይሆን የመጪውን ጊዜ የጋራ መዳረሻ የሚወስን ቁልፍ ጉዳይ በመሆኑ፤ ጽንፍ ከያዙ እሳቤዎች ወደ መሃል በመምጣትና በጋራ በመቆም የጋራ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ የሚያስችል ነው፡፡

ብዝኃነትን ተቀብሎ አካታች ትርክት መፍጠር፤ በዜጎች የጋራ ጥረትና እውቀት የሀገርን ሀብት በፍትሃዊነት በመጠቀም ዘላቂ እድገትን ለማረጋገጥ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡

ሀገሪቱን አጽንጾ ያቆየውን የሕዝቡን የጋራ መስዋዕትነት፣ ማኅበራዊ መስተጋብርና አብሮነትን ማክበር፤ ማስቀጠል ይገባል፡፡

ይህ የወል ትርክት ግንባታ ሀገርን የሚያሻግር፣ የሕግ የበላይነትን፣ እኩልነት እና ፍትሕን ማዕከል ያደረገ እንዲሆን ተቋማዊ ከለላን ይሻል፡፡

ልዩነቶችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምና ልማትን እውን ለማድረግ፤ ብዝኃነትን ከስጋት ምንጭነት አላቅቆ የጥንካሬ ምንጭ ማድረግ አስፈላጊ ነው።

በትዕግስት ግዛቸው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.