Fana: At a Speed of Life!

ዲጂታል ፋይናንስ – የኢትዮጵያ የግብይት ምሕዳር ለውጥ ማሳያ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ኢትዮጵያ ዲጂታል ሥርዓት እየዘረጋች ነው ሲባል ከኢንተርኔትና ቴሌኮም መሠረተ ልማት መስፋፋት የዘለለ ነው።

የማኅበረሰብን የዕለት ተዕለት ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እየቀየረ ያለና የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን እየታየበት ያለው አንዱ መስክ የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት ነው፡፡

ኢትዮጵያ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ግብይትና የገንዘብ ዝውውሮች የሚካሄዱት ጥሬ ገንዘብን መሠረት ባደረገ የእጅ በእጅ መልኩ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ይህ ዓይነት የግብይት ሥርዓት አስተማማኝነቱና ደህንነቱ ጥያቄ ውስጥ የነበረ ሲሆን÷ የዜጎችን ገንዘብ ለብክነትና ለስርቆት የሚዳርግም ነው፡፡

 

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ባህላዊ የነበረውን የግብይት አሠራር በመቀየር የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት አጠቃቀምን በስፋት እየተገበረች ትገኛለች፡፡

በንግድ ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ ነጋዴዎች ቀደም ሲል ብድር ለማግኘትና ክፍያዎችን ለመቀበል እንዲሁም ለማስተላለፍ የነበረባቸውን ተግዳሮቶች ስልካቸው ላይ በሚገኙ የተለያዩ የዲጂታል ፋይናንስ መተግበሪያዎችን በመጠቀም በአነስተኛ ክፍያ በአጭር ጊዜ ቀልጣፋ አገልግሎት ማግኘት ችለዋል፡፡

 

በተጨማሪም የባንክ ቅርንጫፎች በሌሉባቸው አካባቢዎች የሚገኙ አርሶ አደርና አርብቶ አደሮች በሞባይል ስልኮቻቸው አማካኝነት የገንዘብ ዝውውር ማካሄድና ለግብርና ምርቶቻቸው ክፍያ በቀጥታ እንዲከፍሉ እና እንዲቀበሉ አስችሏቸዋል፡፡

 

የመንግሥት ተቋማት ዲጂታላይዝድ የአሠራር ሥርዓትን መከተላቸው ግልጽና ቀልጣፋ እንዲሁም ከሙስና የፀዳ አሠራርን ለመተግበር የፋይናንስ ሥርዓቶች የጎላ አስተዋፅኦን እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡

 

ይህም የፋይናንስ አብዮት የቴክኖሎጂ ፈጠራዎችንና ስታርት አፖችን የሚያበረታታ አዲስ ምዕራፍን የከፈተ ከመሆኑ ባሻገር በተለያዩ ዘርፎች በቴክኖሎጂ የተደገፈ አገልግሎት የሚሰጡ ድርጅቶች እንዲስፋፉ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥሯል፡፡

የዲጂታል ፋይናንስ ዘርፉን አቅም በይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ዜጎችን በማስተማር፣ የሳይበር ደህንነትን በማረጋገጥ፣ የቴሌኮም መሠረተ ልማቶችን ለማጠናከር እየተሰራ ሲሆን ÷ በዲጂታል ዘርፍ ዕውቀትና ክህሎትን ማጎልበት ከዜጎች ይጠበቃል፡፡

በመሆኑም ለዲጂታል ኢትዮጵያ እውን መሆን የገንዘብ ዝውውርን የሚያቃልል፣ የንግድ ፍሰትን የሚያሳልጥ እንዲሁም የኢኮኖሚ እኩልነትን የሚያረጋግጠውን የፋይናንስ ሥርዓት bዲጂታል ቴክኖሎጂ መደገፍ ይገባል፡፡

 

በቤተልሔም ግርማ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.