የአፍሪካ የድሮን ኃይል – ኢትዮጵያ!
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2019 (ኤፍ ኤም ሲ) ወቅቱ የክረምቱ ጭጋጋማ አየር ተገልጦ ተናፋቂዋ የመስከረም ፀሃይ የወጣችበት ዕለት፤ ልክ የዛሬ ዓመት ነበር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በኤሮ አባይ ድሮን ማምረቻ የተገኙት።
በዚያ ወቅት ለንግድ አገልግሎት ከሚውሉት፤ ግዳጅ የመፈፀም አቅም እስካነገቡ ድሮኖች ድረስ በሀገር ልጆች የእጅ ውጤቶች የሚመረትበትን ማዕከል ጎብኝተዋል።
በወቅቱ ከመገናኛ ብዙሃኑ ጋር በነበራቸው ቆይታ ከዚሁ የድሮን ቴክኖሎጂ ጋር አያይዘው በአስረጂነት የጠቀሱት ሕንድን ነበር።
ሕንድ ለምን?
በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር ከ1950ዎቹ በኋላ በድህረ 2ኛው የዓለም ጦርነት ወቅት፤ የደቡብ እስያዊቷ ሀገር ሕንድ ቁስል የነበረው ድህነት ነው።
ድህነት የሚወልደው ብሔራዊ ውርደት፥ ኒውደልሂ ልትቀለብሰው የምትፈልገው ስድቧ ነበር።
እናም በወሰደቻቸው የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና ብሔራዊ ክብር ባቀጣጠለው እድገት እጅግ ፈጣን በሆነ መልኩ ኢኮኖሚው ወደ ፊት ይስፈነጠር ጀመር።
ከጎረቤት ፓኪስታን ብዙ ፈተና ያለባት፤ ደግሞም እንደቀደምት ሀገርነቷ በሚገባት የክብር ቦታ ያልተገኘችው ሕንድ፤ እያደገ የመጣውን ኢኮኖሚዋን ብቻ አንጠልጥላ ወደ ዓለም የውድድር ሜዳ አልተቀላቀለችም።
ይልቁንም መከላከያዋንም በምጣኔ ሀብቱ ትሩፋቱ የማሳደግ ህልሟን ይዛ ቀጠለች፤ ይህም ተሳካላት።
ዛሬ ሀገሪቱ በደቡብ እስያ ከሚገኙ ሀገራት በወታደራዊ አቅሟ ቀዳሚዋ፤ በዓለም ታላቅ መከላከያን ከገነቡ ሀገራት ደግሞ 4ኛ ደረጃ ላይ ተቀመጠች፤ ኢኮኖሚው የመከላከያ አቅሙን ይዞት አብሮ መጠቀ።
ምናልባትም በቀጣዮቹ 4 ዓመታት ዓለማችን ላይ የመከላከያ ትጥቅና መሳሪያን ለሌሎች ሀገራት በመላክ ከቀዳሚ 6 ሀገራት ተርታ አንዷ ለመሆን ደፋ ቀና እያለች ትገኛለች፤ ትንበያዎችም ሕንድን ከዚህ ጉዞዋ ወደ ኋላ የሚጎትታት ኃይል እንደሌለ አመላካች ናቸው።
በርግጥ ያቺ እስያዊት ሀገር ዛሬ አስደናቂ ለውጥ ላይ የሚገኘው አምራች ዘርፏን በመከላከያ ዘርፍ ላይ ከተሰማሩ ኩባንያዎቿ ንግድ ነጥላዋለች ማለትም አይደለም።
ዓለማችን በየዓመቱ ይህንን የመከላከያ ዘርፍና ትጥቅ ገበያን በ2 ነጥብ 8 ትሪሊየን ዶላር በሆነ ግብይት እያንቀሳቀሰችው ነው።
በዚህ ዘርፍ ውስጥ ካሉ 100 የዓለማችን ኩባንያዎች ውስጥ ደግሞ 3ቱ የሕንድ መከላከያ ኩባንያዎች ናቸው።
ይህ ብቻም አይደለም፤ እኚህ 3 ኩባንያዎች ዓለም ከተገበያየችው የ2 ነጥብ 8 ትሪሊየን ዶላር ውስጥ የ7 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ድርሻቸውን ዘግነዋል።
ምንም እንኳ ይህ ገንዘብ ከሀገሪቱ እድገት አንፃር ገና የሚባል ገንዘብ ቢሆንም በየዓመቱ ግን ከ8 በመቶ በላይ እድገት እያስመዘገበ የቀጠለ እድገት ነው፤ የኢኮኖሚ መነሳት የመከላከያ አቅም አብሮ ማደግ የሚሆነው እንግዲህ በዚህ አመክንዮ ነው፡፡
ኢትዮጵያስ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የኤሮ አባይ ድሮን ማምረቻን በጎበኙበት ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ እመርታ ከሚያሳዩ በጣት ከሚቆጠሩ ሀገራት መካከል አንዷ ሆኗለች፡፡
በዚሁ ንግግራቸው “አጠቃላይ የኢኮኖሚ ጉዞው ትክክለኛውን መስመር ሲይዝ ብልፅግናን ማረጋገጥ የሚያስብ ሀገርና ህልም ያላቸው ሰዎች ቀጥለው ሊያስቡበት የሚገባው ጉዳይ፤ ወታደራዊ አቅም ነው” በማለት አስረድተዋል፡፡
“እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ሀገራት ኢኮኖሚውን ከወታደራዊ አቅም ጋር አሰናስለው ማስኬድ ካልቻሉ፤ በአቅም ማነስ ምክንያት ብዙ የተደከመበት ኢኮኖሚ ሊወድቅ ይችላል” ነበር ያሉት፡፡
የሕንድ የቀደመ ልዕልና እና ሀገራዊ ክብርን የማስጠበቅ ጉዞ እንደ ኒውደልሁ ሁሉ በቀደመ ስልጣኔዋ ገናና፤ አሁን ደግሞ መስፈንጠር በጀመረው ኢኮኖሚያዊ የእድገት አምሳያዋ ከሆነችው ኢትዮጵያ ታሪክ ጋር ይቀራረባል።
የብዙ ሺህ ዘመናት የሀገረ መንግሥት ታሪክ ባለቤቷ ኢትዮጵያ፤ ክብርኗንም ስሟንም ሊመጥን የሚችል የቴክኖሎጂ ጉዞ ላይ መሆኗን ከሚያሳዩ እውነታዎች መካከል አንዱ ይኸው የድሮን ቴክኖሎጂ አቅም ነው።
በጦርነት ወቅት ዒላማን በተሳካ ሁኔታ ከሚያጠፉ ድሮኖች ጀምሮ ለስለላ የሚውሉ በእጅ የሚያዙ፣ በኪስ የሚገቡ አልያም በቦርሳ የሚንጠለጠሉ አነስተኛ ድሮኖች እንዲሁም የንግድ ድሮኖች በዚህ የድሮን ማምረቻ ውስጥ እየተመረቱ ይገኛሉ፡፡
በሀገራችን ተሰናድቶ በነበረው ዓለም አቀፉ የኢንተርኔት ጉባዔ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የአዲስ አበባን ሰማይ ካደመቁበት ዕለት አንስቶ፤ በዘንድሮው የአዲስ ዓመትና የጊፋታ በዓላት ላይ የተለያዩ መልዕክቶችን ይዘው በሰማይ ላይ የሚደምቁ ድሮኖችን መመልከት ተችሏል፡፡
ይህ የሀገር ከፍታ የማይሆን ይመስል የነበረውን ሩቅ ህልም አቅርቦ ዛሬ ኢትዮጵያ ለቅኝት፤ ግዳጅ ለመፈፀምና ለንግድ የሚውሉ ድሮኖችን በብዛትና በተለያዩ ቦታዎች የማምረት አቅም ፈጥራለች።
ወደ ኋላ እንመልሳችሁ!
ልክ የዛሬ ዓመት የክረምቱ ጭጋግ ገፍፎ፤ የመስከረሟ ደማቅ ፀሃይ በወጣችበት ዕለት፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በድሮን ማመረቻው ያደረጉትን ጉብኝት ሲያጠናቀቁ ለመገናኛ ብዙሃኑ በሰጡት አስተያየት መቋጫ ላይ እንዲህ አሉ፡-
“በእርሻ፣ በማዕድን እንዲሁም በሌሎች ዘርፎች ያመጣነው ውጤት በእንዲህ አይነት አቅም ካለተደገፈ ብዙ ባንዳና ባዳ ባለበት አካባቢ ዘመንን መዋጀት አይቻልም፤ እናም አቅም ወሳኝ ነው” ነበር ያሉት፡፡
በነቢዩ ይርጋለም